png-logo-white   GREAT ETHIOPIAN RUN

English Arabic Chinese (Simplified) French German Japanese Norwegian Russian Spanish

አልማዝ የጥሩነሽን የለንደን ገድል ስትደግም ገንዘቤ በመካከለኛ ርቀት ፈይሳ በማራቶን የመጀመሪያ የሆኑ ሜዳልያዎችን አስገኝተዋል   

በሪዮ ኦሊምፒክ ከነሐሴ 6 ጀምሮ በጆአኦ ሀቫላንጅ ኦሊምፒክ ስታዲየም መም እንዲሁም በጎዳና ላይ ሲካሄዱ የሰነበቱት የአትሌቲክስ ፉክክሮች ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ ዳግም ወደኦሊምፒክ ተሳትፎ ከተመለሰችበት የ1992ቱ የባርሴሎና ኦሊምፒክ ወዲህ ዝቅተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ቁጥር በማስመዝገብ አጠናቃለች፡፡  


14080993 10154474402688637 367612639 n14111867 10154474402653637 1316548174 n

 

1 ወርቅ 2 ብር እና 5 የነሐስ ሜዳልያዎችን ይዞ ላጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን አልማዝ አያና በሴቶች 10 ሺህ ሜትር ብቸኛውን የወርቅ ሜዳልያ ድል ስታስገኝ ገንዘቤ ዲባባ በሴቶች 1500ሜ. እና ፈይሳ ሌሊሳ በወንዶች ማራቶን የብር፣ ጥሩነሽ ዲባባ በሴቶች 10 ሺህ ሜትር፣ ታምራት ቶላ በወንዶች 10 ሺህ ሜትር፣ ማሬ ዲባባ በሴቶች ማራቶን፣ አልማዝ አያና በሴቶች 5 ሺህ ሜትር እና ሐጎስ ገብረሕይወት በወንዶች 5 ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳልያዎቹን አስገኝተዋል፡፡ አልማዝ አያና በሴቶች 10 ሺህ እና 5 ሺህ ሜትር ባስመዘገበችው የወርቅ እና ነሐስ ሜዳልያ ድል ጥሩነሽ ዲባባ በለንደን 2012 ላይ የሠራችውን ገድል የደገመች ሲሆን ገንዘቤ ዲባባ በሴቶች 1500ሜ. ያስገኘችው የብር ሜዳልያም በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በመካከለኛ ርቀት የተመዘገበ የመጀመሪያው የሜዳልያ ስኬት ሆኗል፡፡ ምንም እንኳ በማራቶን ከዚህ ቀደም የኦሊምፒክ ወርቅ እና ነሐስ ሜዳልያ ድሎች የነበሩን ቢሆንም ፈይሳ ሌሊሳ በወንዶች ማራቶን የተሳትፎ ታሪካችን የመጀመሪያ የሆነውን የኦሊምፒክ ማራቶን የብር ሜዳልያ አስገኝቷል፡፡

14088749 10154474400563637 2000272174 n

ፍፃሜው እንደጅማሬው መሆን ባልቻለው የሪዮ ኦሊምፒክ ተሳትፎ የወርቅ ሜዳልያ እንደምናገኝ ከፍተኛ ግምት በሰጠናቸው ውድድሮች ላይ ጭምር በሌሎች ተፎካካሪዎች የተቀደምን ቢሆንም አትሌቶቻችን የአትሌቲክስ ውድድሮች ቁንጮ በሆነው የኦሊምፒክ ፉክክር ላይ የአቅማቸውን ጥረው ላስገኙልን ሜዳልያዎች እና ለነበራቸው ተሳትፎ ከፍተኛውን ክብር መስጠት ይገባናል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም ውድድር በመጣ ቁጥር በስሜታዊነት እና በስማ በለው ከሚነገሩ የሆይ ሆይታ አስተያየቶች በዘለለ በተጨባጭ ጥናት ላይ ተመስርተን ሀገራችን በዓለም ዙሪያ ስሟ በበጎ ጎኑ እንዲነሳ ማድረግ የቻለው የአትሌቲክስ ስፖርት ወደተለመደው ውጤታማነቱ እንዲመለስ በርትተን መስራት ግድ ይለናል፡፡

በመጨረሻዎቹ ሶስት ቀናት ኢትዮጵያውያን ሜዳልያ ያስገኙባቸው ውድድሮች

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በመጨረሻዎቹ ሶስት ቀናት ውድድሮች ለአሸናፊነት ሲጠበቁ በነበሩባቸው የሁለቱም ፆታዎች የ5000ሜ. የፍፃሜ ፉክክር የነሐስ ሜዳልያ እንዲሁም ኬንያዊው ኤሉድ ኪፕቾጌ ሲጠበቅ በነበረበት የወንዶች ማራቶን የብር ሜዳልያ ድልን አስመዝግበዋል፡፡ አልማዝ አያና በሴቶች ሀጎስ ገብረሕይወት በወንዶች የ5000ሜ. ሜዳልያዎቹን ያስገኙ አትሌቶች ናቸው፡፡ 

የዓለም ሪኮርድ በመስበር ጭምር የ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ የሆነችው አልማዝ አያና በሴቶች 5000 ሜትር ውድድርም የወርቅ ሜዳልያውን እንደምትወስድ ከፍተኛ የቅድሚያ ግምት አግኝታ የነበረ ቢሆንም ግምቱ አልተሳካም፡፡ በፍፃሜው ውድድር በመጀመሪያዎቹ ሶስት ዙሮች ጃፓናዊቷ ኡሀራን ስትከተል የቆየችው አልማዝ በተለመደ የአሯሯጥ ስልቷ በመጠቀም ስምንት ዙር እየቀራት ፍጥነቷን ጨምራ ወጥታ ሶስቱን ኬንያውያን (ቪቪያን፣ ኦቢሪ እና ቼሮኖ) በሰፊ ልዩነት ብትመራም በመሀከላቸው በነበረው ሰፊ ልዩነት ተስፋ ባለመቁረጥ እና በመተጋገዝ ልዩነቱን ማጥበብ የቻሉት ቪቪያን እና ኦቢሪ ውድድሩ ሊጠናቀቅ 700ሜ. ሲቀር አልማዝ ላይ በመድረስ አልፈዋት ለመሄድ ችለዋል፡፡ በመጨረሻም ቪቪያን ቼሪዮት 14፡26.17 በሆነ አዲስ የኦሊምፒክ ሪኮርድ ሰዓት የወርቅ ሜዳልያውን ስትወስድ ሌላኛዋ ኬንያዊ ሔለን ኦቢሪ (14፡29.77) የብር አልማዝ አያና (14.33.59) የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊ ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያን ወክለው የተወዳደሩት ሰንበሬ ተፈሪ (14፡43.75) አምስተኛ እንዲሁም አባበል የሻነህ (15፡18.26) አስራ አራተኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡ 

በሙሉ የራስ መተማመን ስሜት የወርቅ ሜዳልያውን እንደምታሸንፍ አስባ በገባችበት ውድድር ሶስተኛ ሆና ማጠናቀቋ እጅግ እንዳበሳጫት የጠቀሰችው አልማዝ አያና ከአምስት ሺህ ሜትሩ ውድድር በኋላ ‹‹ወደውድድሩ ስገባ ሙሉ ጤነኛ ነበርኩ፡፡ አምስት ሺህ ሜትር በዋናነት የምሮጠው ርቀት በመሆኑም ግቤ የወርቅ ሜዳልያ ማምጣት ነበር፡፡ ሆኖም ውድድሩ ሊያልቅ አራት ዙር ሲቀር ድካም ሲሰማኝ እንደማላሸንፍ አረጋገጥኩ፡፡ ኬንያውያኑ ተወዳዳሪዎች ሲያልፉኝ ብቻ ነው ያየሁት፡፡ የውድድሩን የመጨረሻ መስመር እስካልፍ ድረስም የሆነውን ነገር ማመን አልቻልኩም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሮጥኩባቸው በሁለቱም ርቀቶች ወርቅ ይፈልግ ነበር፡፡ በውጤቱ በጣም እንደተከፋም እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስለዚህ በጣም ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ በራሴም በኩል በጣም አዝኛለሁ›› ብላለች፡፡

የውድድሩ አሸናፊ የሆነችው ኬንያዊቷ ቪቪያን ቼሪዮት ምንም እንኳ ከውድድሩ በኋላ በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገበርነው ከውድድሩ በፊት ያቀድነውን ነው ብትልም ውድድሩ እንዳለቀ በሰጠችው አስተያየት ‹‹ወደውድድሩ የገባሁት የብር ሜዳልያን አልሜ ነበር፡፡ ሆኖም ወደውድድሩ ከገባን በኋላ ስንሮጥ የነበረው ከሔለን ኦቢሪ ጋር እየተመካከርን ነበር፡፡ እናም ኦቢሪ አልማዝ ፍጥነቷን ጨምራ ስትወጣ ተከትለን በመውጣት እራሳችንን ማቃጠል እንደሌለብን እና ወደመጨረሻ ላይ ፍጥነቷን ስትቀንስ ደርሰን ለመያዝ ተስፋ ሳንቆርጥ መጓዝ እንዳለብን በመንገር አበርትታኛለች፡፡ በዚህ መልኩ ሮጠንም ውጤቱን ልናሳካ ችለናል›› ብላለች፡፡ 

በሪዮ ኦሊምፒክ የወንዶች 5000ሜ. የፍፃሜ ፉክክር ሞ ፋራህ በ13፡03.30 ቀዳሚ ሆኖ የወርቅ ሜዳልያውን ሲወስድ ትውልደ ኬንያዊው የአሜሪካ ሯጭ ፖል ኪፕኬሞይ ቼሊሞ በ13፡03.90 የብር ሜዳልያ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ሀጎስ ገ/ሕይወት በ13፡04.35 ሶስተኛ ወጥቶ ለኢትዮጵያ የነሐስ ሜዳልያን አስገኝቷል፡፡ ትውልደ ሶማሊያዊው እንግሊዛዊ ሞ ፋራህ በኦሊምፒክ ውድድር በተከታታይ ለሁለተኛ ግዜ እንዲሁም ባጠቃላይ በአራት ተከታታይ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በ10 ሺህ እና 5 ሺህ ሜትር የድርብ ድል ባለቤት መሆኑን ባረጋገጠበት የሪዮ ኦሊምፒክ የወንዶች 5000ሜ. ፉክክር ላይ ደጀን ገብረመስቀል በ13፡15.91 አስራ ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ አራተኛ ወጥቶ የነበረው ኢትዮጵያዊው ሙክታር እድሪስ በውድድሩ ላይ ፈፅሟል በተባለው ጥፋት በአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ የውድድር ሕግ ቁጥር 163.3ቢ መሰረት ውጤቱ መሰረዙ (ዲስኳሊፋይድ መሆኑ) ተገልፃôል፡፡ ይህ ውድድር እንደተጠናቀቀ ሁለተኛ ሆኖ የጨረሰው አሜሪካዊው ኪፕኬሞይ ቼሊሞ እና አራተኛ የወጣው ካናዳዊ መሐመድ አህመድ ውጤትም እንደተሰረዘ እና ሀጎስ ገ/ሕይወት የብር ሜዳልያ አግኝቶ እንደነበረ ተገልፆ የነበረ ቢሆንም ሁለቱ አትሌቶች ያቀረቡት የይግባኝ ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ውጤታቸው ተመልሶ እንዲፀድቅላቸው ተደርጓል፡፡ 

ኢትዮጵያውያኑ ሀጎስ ገ/ሕይወት እና ደጀን ገብረመስቀል እስከ ሰባተኛው ዙር ድረስ ውድድሩን በቅብብሎሽ በማፍጠን ሞ ፋራህን ለመቁረጥ (የመጀመሪያውን ዙር በ62.04፣ ሁለተኛውን 63.72፣ ሶስተኛውን 63.54፣ አራተኛውን 63.07፣ አምስተኛውን 63.98 ሄደዋል) ያደረጉት ጥረት ስኬታማ ሳይሆን ቀርቶ ሞ ፋራህ ከስምንተኛው ዙር በኋላ የውድድሩን መሪነት ሊረከብ እና የመጨረሻዎቹን አራት ዙሮች ሊመራ ብሎም በመጨረሻው ዙር ከሐጎስ እና አሜሪካዊው ቼሊሞ ጋር ያደረገውን ፉክክር መቶ ሜትር ሲቀረው ቀድሞ በመሄድ ሊያሸንፍ በቅቷል፡፡ ሞ ፋራህ 11ኛውን ዙር በ59.82 ሲሸፍን የመጨረሻውን አራት መቶ ሜትር በ52.83 ሰከንድ ፍጥነት ሮጧል፡፡ 

ሀጎስ ገ/ሕይወት ከውድድሩ በኋላ ‹‹ትኩረታችንን በሙሉ ሞ ፋራህ ላይ አድርገን የመጀመሪያዎቹን አምስት ዙሮች ከደጀን ጋር እየተቀያየርን እርሱን ለመቁረጥ ያስችለናል ባልነው ፍጥነት ሄደናል፡፡ ነገር ግን ሙከራችን አልተሳካም፡፡ ስለዚህ ወደሁለተኛው አማራጭ በመግባት መጨረሻ ላይ በነበረው ፉክክር ለማሸነፍ ጥሬ አልሆነልኝም፡፡ ነገር ግን በነሐስ ሜድልያ ድሌም ደስተኛ ነኝ›› ብሏል፡፡

በወንዶች 10 ሺህ ሜትር እና 5 ሺህ ሜትር የኦሊምፒክ ድርብ ድልን በተከታታይ ለሁለተኛ ግዜ ማሳካት የቻለው ሞ ፋራህ ከ5 ሺህ ሜትር ድሉ በኋላ ‹‹ያሳካሁትን ድል ለማመን ይከብደኛል፡፡ ሁልግዜም ምኞቴ አንድ ሜዳልያ ስለማሸነፍ ነበር፡፡ ረጅምና አድካሚ ጉዞ ሲሆን ልጆቼን እንኳ የማላይበት ግዜ ይበዛ ነበር፡፡ ከልጆቼ ጋር ማሳለፍ ሳልችል የቀረሁባቸውን ግዜያት መልሼ ማግኘት ባልችልም ያስመዘገብኳቸው ስኬቶች ለእነርሱ የማቀርባቸው ስጦታዎቼ ናቸው፡፡ የዚህ አይነቱን ስኬት የምታልም እና ጠንክረህ የምትሰራ ከሆነ ስኬታማ መሆንህ አይቀርም›› ብሏል፡፡

በአትሌቲክስ ውድድሩ የመጨረሻ ቀን በተከናወነው የወንዶች ማራቶን ፉክክር ኢትዮጵያ በፈይሳ ሌሊሳ (2:09:54) አማካይነት የብር ሜዳልያ ድልን ተቀዳጅታለች፡፡ ከጅምሩ አንስቶ አብዛኛውን ኪሎ ሜትር በዝናብ ታጅቦ በተካሄደው ፉክክር በወቅታዊ ምርጥ ብቃቱ ላይ የሚገኘው ኬንያዊው ኤሉድ ኪፕቾጌ በ2:08:44 አሸናፊ በመሆን ከውድድሩ በፊት ለአሸናፊነቱ የተሰጠው ግምት ትክክል እንደነበር አረጋግጧል፡፡ ኢትዮጵያዊያኑ ለሚ ብርሀኑ እና ፈይሳ ሌሊሳ ከ30ኛው ኪሎ ሜትር በኋላ በፉክክሩ ውስጥ ከቆዩት አራት አትሌቶች መካከል የነበሩ ሲሆን ለሚ ከ32ኛው ኪሎ ሜትር በኋላ ተከትሎ መሄድ ሳይችል ቀርቶ በመጨረሻም በ2:13:29 ሰዓት 13ኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ 

በሪዮ ኦሊምፒክ የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ፉክክር ላይ ተሳትፎ በ27፡08.92 አምስተኛ ሆኖ ካጠናቀቀ በኋላ በማራቶን ውድድሩ ላይም ብርቱ ተፎካካሪ ሆኖ የታየው አሜሪካዊው ጋለን ሩፕ ፈይሳ ሌሊሳ እና ኪፕቾጌ የቀሩበት ፉክክር ከ35ኛው ኪሎ ሜትር በኋላ ወደመጨረሻው ምዕራፍ ሲሸጋገር ፈይሳ ኬንያዊውን እግር በእግር ለመከተል ያደረገው ሙከራ ስኬታማ አልነበረም፡፡ ኪፕቾጌ ፍጥነቱን እየጨመረ በመሄድ አሸናፊ ሆኖ ሲጨርስ ፈይሳም በእርሱ እና በጋለን ሩፕ መካከል የነበረውን ልዩነት አስጠብቆ የብር ሜዳልያ ባለቤት መሆን ችሏል፡፡ በ2፡10፡05 ሶስተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊ የሆነው ጋለን ሩፕ በአሜሪካ የኦሊምፒክ ታሪክ በ10 ሺህ ሜትር እና በማራቶን ሜዳልያ ማሸነፍ የቻለ የመጀመሪያው አትሌት ሆኗል፡፡ 

ኢትዮጵያዊው ተስፋዬ አበራ 24ኛው ኪሎ ሜትር ላይ ሲደርስ በህመም ምክንያት ውድድሩን ለማቋረጥ የተገደደ ሲሆን ኬንያውያኑ ስታንሊ ቢዎት እና ዌስሊ ኮሪርም ውድድሩን ማጠናቀቅ ሳይችሉ ከቀሩት መካከል ሆነዋል፡፡ ከአራት አመት በፊት በለንደን የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ የነበረው ኡጋንዳዊው ስቴፈን ሮቲች በ2፡13፡32 አስራ አራተኛ ሆኖ ጨርሷል፡፡     

ፈይሳ ሌሊሳ ከብር ሜዳልያ ድሉ በኋላ ‹‹ውድድሩ በጣም ጥሩ ውድድር ነው፡፡ ዝናብ እየዘነበ የነበረ በመሆኑ ግን አስፓልቱ ትንሽ እግሬን ያዝ እንዲያደርገኝና እንዲከብደኝ አድርጓል፡፡ መጨረሻ ላይ የኪፕቾጌን ፍጥነት ተከትዬ መሄድ ባልችልም አሜሪካዊው ጋለን ሩፕ ይቀድመኛል የሚል ስጋት ግን አልነበረኝም›› ብሏል፡፡  

ኤሉድ ኪፕቾጌ ‹‹ለመውጣት ያሰብኩት 30ኛው ኪሎ ሜትር ላይ የነበረ ቢሆንም ፉክክሩ እስከ 35ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ እንድቆይ አስገድዶኛል፡፡ ይህ ድል የሩጫ ሕይወቴ ምርጡ ድል ሜዳልያውም በሩጫ ሕይወቴ ያገኘሁት ትልቁ ሽልማት ነው›› ብሏል፡፡

በሪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በአጠቃላዩ የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ 44ኛ በአትሌቲክሱ ብቻ ደግሞ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ አጠናቀለች፡፡       

Share