png-logo-white   GREAT ETHIOPIAN RUN

English Arabic Chinese (Simplified) French German Japanese Norwegian Russian Spanish

ብራዚሏ ሪዮ ደ ጃኔይሮ ከተማ አስተናጋጅነት እየተከናወነ ባለው 31ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የአትሌቲክስ ፉክክር አምስተኛ ቀን ውሎ ከተከነናወኑት የፍፃሜ ውድድሮች አንዱ የሴቶች 1500ሜ. ሲሆን ገንዘቤ ዲባባ በኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕዬጎን ተቀድማ የብር ሜዳልያ ባለቤት ሆናለች፡፡ በንፅፅር በማጣሪያው ላይ ከተመዘገበው በዘገየ ሰዓት በተጠናቀቀው የፍፃሜ ፉክክር የመጀመሪያው ዙር ቀርፋፋ የነበረ ሲሆን ገንዘቤም ይህን ዙር ከተፎካካሪዎቿ በስተኋላ ሆና ስትከተል ቆይታለች፡፡ በቅድመ ውድድር ዕቅዷ የመጨረሻ ሩጫዋን ስድስት መቶ ሜትር ላይ ልትጀምር አስባ እንደገባች የጠቀሰችው ገንዘቤ ከብር ሜዳልያ ድሏ በኋላ ‹‹በውድድሩ ላይ ቦታ ለመያዝ በነበረው ፉክክር የመጨረሻ ሩጫዬን ቀደም ብዬ 700ሜ. እየቀረኝ ለመጀመር ተገድጃለሁ፡፡ በጉዳት ምክንያት ብዙ ዝግጅት ማድረግ አልቻልኩም እንደዛም ሆኖ ለሀገሬ ብር ሜዳልያ ማምጣት ችያለሁ›› ያለች ሲሆን አሰልጣኟ ጀማ አደን ከአበረታች መድኃኒት ጋር በተያያዘ መጠርጠሩ በእርሷ ላይ ስለፈጠረው ተፅኖ ስታወራም ‹‹በጀማ ጉዳይ በተለይ በሀገራችን ሚዲያዎች ስሜ ሲነሳ ነበር፡፡ ጀማ ተጠረጠረ ማለት እኔ ተያዝኩ ወይም ተጠረጠርኩ ማለት አይደለም፡፡ እኔን ከጀማ ጋር የሚያገናኘኝ ስራ ነው እንጂ ስለዚህ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ይህ ጉዳይ በሀገራችን ሚዲያዎች ትንሽ ጫና አሳድሮብኛል›› ብላለች፡፡ ገንዘቤ በሪዮ ኦሊምፒክ ያሳካችው የብር ሜዳልያ ድል በኢትዮጵያ የ60 ዓመት የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በመካከለኛ ርቀት የተገኘ የመጀመሪያው ሜዳልያ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የኢትዮጵያ የእስከዛሬ የሜዳልያ ድሎች በሁለቱም ፆዎች በ50000ሜ.፣ 10000ሜ.፣ ማራቶን እና 3000ሜ. መሰናክል የተገኙ የነበሩ ሲሆን ገንዘቤ በሪዮ ደ ጃኔይሮ ያመጣችው የ1500ሜ. የብር ሜዳልያ ስኬት የተመዘገበባቸውን የውድድር አይነቶች ቁጥር በአንድ ከፍ ያደረገም ነው፡፡

የ1500ሜ. ወርቅ ሜዳልያ አሸናፊዋ ፌይዝ ኪፕዬጎን በበኩሏ ‹‹አሸንፋለሁ ብዬ አልጠበቅኩም ነበር፡፡ የመጀመሪያ የኦሊምፒክ ሜዳልያዬን በማሸነፌ ያውም ወርቅ እጅግ በጣም ደስተኛ ሆኛለሁ፡፡ ገንዘቤ በመጨረሻዎቹ 800ሜ. ላይ ተፈትልካ እንደምትሄድ አውቅ ነበር፡፡ በደንብ ተዘጋጅቼበት ስለነበር ተከትያት እንደምወጣ በራስ የመተማመን ስሜቱ ነበረኝ፡፡ በውድድሩ ላይ ምንም አይነት አስቸጋሪ ሁኔታ አልነበረም፡፡ የመጀመሪያው ዙር ዝግ ያለ የነበረ መሆኑም ያን ያህል ከባድ ፈተና እንደማይገጥመኝ እንዳውቅ እና በመጨረሻ ለሚኖረው ለየትኛውም አይነት ፈጣን ሩጫ ዝግጁ እንድሆን አድርጎኛል›› ብላለች፡፡

ከፈይዝ ኪፕዬጎን (4:08.92) እና ገንዘቤ ዲባባ (4:10.27) በመቀጠል አሜሪካዊቷ ጄኒፈር ሲምፕሰን በ4:10.53 ውድድሩን በሶስተኛነት አጠናቃ የነሐስ ሜዳልያውን ወስዳለች፡፡ ለፍፃሜው ተፎካካሪነት በቅተው የነበሩት ኢትዮጵያኑ ዳዊት ስዩም (4:13.14) እና በሱ ሳዶ (4:13.58) በቅደም ተከተል ስምንተኛ እና ዘጠነኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡  

genzebe dibaba main

የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የማጣሪያ ውድድሮች ተሳትፎና ሌሎች የፍፃሜ ውድድሮች 

በሪዮ ኦሊምፒክ የአራተኛ ቀን ውሎ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በ3000ሜ. መሰናክል በወንዶች የማጣሪያ በሴቶች ደግሞ የፍፃሜ ውድድሮች ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን በሁለቱም ውድድሮች ስኬታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በወንዶች የ3000ሜ. ማጣሪያ ላይ ከተሳተፉት በምድብ አንድ የሮጠው ኃይለማሪያም አማረ (8:35.01) ስምንተኛ በምድብ ሁለት የተወዳደረው ጫላ በዮ (8:32.06) ሰባተኛ ሆነው በመጨረስ ሳያልፉ ሲቀሩ በምድብ ሶስት የተወዳደረው ታፈሰ ሰቦቃ ዲስኳሊፋይድ ሆኗል፡፡ በወንዶች 3000ሜ. መሰናክል የፍፃሜ ውድድር ኬንያዊው ኮንሴለስ ኪፕሩቶ የኦሊምፒክ ሪኮርድ በሆነ 8፡03.28 ሰዓት የወርቅ ሜዳልያ ሲወስድ አሜሪካዊው ኢቫን ጃገር (8:04.28) እና ኬንያዊው ኢዝኬል ኪምቦይ (8:08.47) በቅድም ተከተላቸው መሰረት የብር እና ነሐስ ሜዳልያ ባለቤት ሆነዋል፡፡

የሴቶች 3000ሜ. መሰናክል ፍፃሜ ኢትዮጵያ የሜዳልያ ደረጃ ውስጥ እንደምትገባ ተስፋ ከተደረገባቸው ውድድሮች አንዱ የነበረ ቢሆንም ትውልደ ኬንያዊቷ የባህሬይን ተወካይ ሩት ጄቤት የኤሪአ ሪኮርድ በሆነ 8፡59.75 አንደኛ፣ ኬንያዊቷ ሀይቪን ኪገን በ9፡07.12 ሁለተኛ እና አሜሪካዊቷ ኤማ ኮበርን የኤሪአ ሪኮርድ በሆነ 9፡07.63 ሶስተኛ ወጥተው የሜዳልያ ደረጃዎቹን ተቆጣጥረዋል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ለሜዳልያ ትጠበቅ የነበረችው ሶፊያ አሰፋ ለራሷ የዓመቱ ምርጥ በሆነ 9:17.15 አምስተኛ፤ በማጣሪያው ባሳየችው አይበገሬነት የብዙዎችን ትኩረት የሳበችው እቴነሽ ዲሮ አስራ አምስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል፡፡               

መሐመድ አማን ሳያልፍ በቀረበት የወንዶች 800ሜ. ፍፃሜ ኬንያዊው ዴቪድ ሩዲሻ የራሱ የዓመቱ ምርጥ በሆነ 1:42.15 ሰዓት የለንደን ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤትነት ክብሩን ማስጠበቅ የቻለ ሲሆን አልጄሪያዊው ቶፊቅ ማክሉፊ (1:42.61) እና አሜሪካዊው ክሌይተን መርፊ (1:42.93) የብር እና ነሐስ ሜዳልያ አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡ ዴቪድ ሩዲሻ ከድሉ በኋላ በሰጠው አስተያየት የቡድን አጋሩ ሊተገብሩ የተመካከሩትን ታክቲክ ባለመተግበር ውጤቱን ሊያበላሽበት መሞከሩ እንዳላስደሰተው በመናገር የተሰማውን ቅሬታ ይፋ አድርጓል፡፡

በአምስተኛው ቀን የአትሌቲክሱ የውድድር ውሎ ከተከናወኑ የማጣሪያ ውድድሮች መካከል ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተሳተፉባቸው የሴቶች 5000ሜ. እና የወንዶች 1500ሜ. የሚገኙ ሲሆን በማጣሪያዎቹ ላይ የተሳተፉት አትሌቶች በሙሉ ወደተከታዩ ውድድር ለመሸጋገር ያበቃቸውን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ በአትሌቲክስ ውድድሩ መክፈቻ ዕለት የዓለም ሪኮርድ በመስበር ጭምር ያሸነፈችው አልማዝ ሁለተኛ የወርቅ ሜዳልያ እንደምታስመዘግብበት በሚጠበቀው የሴቶች 5000ሜ. ማጣሪያ ከምድብ ሁለት 15፡04.35 በሆነ ሰዓት ተፎካከሪዎቿን በሰፊ ልዩነት ቀድማ አንደኛ ሆና ስታጠናቅቅ ሰንበሬ ተፈሪ በ15፡17.43 ሁለተኛ ሆና ጨርሳ ሁለቱም ለፍፃሜው አልፈዋል፡፡ በምድብ አንድ ተወዳድራ በ15፡24.38 ስምንተኛ ሆና ያጠናቀቀችው አባበል የሻነህ በፈጣን ሰዓት ካለፉት አምስት አትሌቶች አንዷ በመሆን ፍፃሜውን ተቀላቅላለች፡፡ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ሜዳልያዎችን እንደምታስመዘግብበት የሚጠበቀው የሴቶች 5000ሜ. የፍፃሜ ውድድር ዓርብ ከለሊቱ 9፡40 ላይ የሚከናወን ይሆናል፡፡

አማን ወጤ በጉዳት ምክንያት በተደለደለበት ምድብ ውድድሩን መጀመር ባልቻለበት የወንዶች 1500ሜ. ማጣሪያ በምድብ ሁለትና ሶስት የሮጡት መኮንን ገ/መድህን እና ዳዊት ወልዴ ለግማሽ ፍፃሜው አልፈዋል፡፡ መኮንን ገ/መድህን በ3:47.33 ከምድብ ሁለት ስድስተኛ ወጥቶ በቀጥታ ሲያልፍ ከምድብ ሶስት በ3:39.29 አስረኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ዳዊት ወልዴ በፈጣን ሰዓት ካለፉት ስድስት አትሌቶች አንዱ ሆኖ ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል፡፡     

ጃማይካዊው ዩሴይን ቦልት በሪዮ የዓለም ሪኮርድን በመስበር ጭምር ማሸነፍ እንደሚፈልግ በገለፀበት የ200ሜ. ወንዶች ማጣሪያ ምድብ ዘጠኝ ዘና ብሎ በማሸነፍ ያለፈ ሲሆን የሀገሩ ልጅ ዮሀን ብሌክም ወደተከታዩ ማጣሪያ ካለፉት መካከል ይጠቀሳል፡፡

የማጣሪያ ውድድሮቹ በስድስተኛው ቀን የጠዋት ፕሮግራም ቀጥለው ኢትዮጵያውያኑ ሀጎስ ገ/ሕይወት፣ ደጀን ገብረመስቀል እና ሙክታር እድሪስ በወንዶች 5000ሜ. ሀብታምነሽ አለሙ ደግሞ በሴቶች 800ሜ. የማጣሪያ ውድድራቸውን በስኬት አጠናቀዋል፡፡ በወንዶች 5000ሜ. በመጀመሪያው ምድብ የተወዳደረው ሀጎስ ገ/ሕይወት በ13:24.65 አንደኛ ሆኖ ሲያልፍ እንግሊዛዊው ሞ ፋራህም ከዚሁ ምድብ በ13:25.25 ሶስተኛ ሆኖ በመጨረስ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል፡፡ ፈጣን በነበረው ሁለተኛው ምድብ የተወዳደሩት ሙክታር እድሪስ (13:19.65) እና ደጀን ገ/መስቀል (13:19.67) ለዩናይትድ ስቴትስ የሚወዳደረው ትውልደ ኬንያዊው ፖል ኪፕኬሞይን (13:19.54) ተከትለው ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመውጣት ለፍፃሜው አልፈዋል፡፡  

ሶስት አትሌቶችን ባሳተፍንተበት የሴቶች 800ሜ. ከምድብ ሶስት የተወዳደረችው በ2:00.13 አራተኛ የወጣችው ጉዳፍ ፀጋዬ እና ከምድብ አምስት በ2:00.21 አምስተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ትግስት አሰፋ ለግማሽ ፍፃሜው ማለፍ ያልቻሉ ሲሆን የራሷን ምርጥ ባሻሻለችበት 1:58.99 ከምድብ አራት ሶስተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ሀብታም አለሙ በፈጣን ሰዓት ካለፉት ስምንት አትሌቶች አንዷ ሆና ግማሽ ፍፃሜውን መቀላቀል ችላለች፡፡ ይህ ዘገባ እስከተፃፈበት ሰዓት ድረስ ኢትዮጵያ በሪዮ ኦሊምፒክ በአልማዝ አያና፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ማሬ ዲባባ እና ታምራት ቶላ አማካይነት ባስመዘገበቻቸው አምስት ሜዳልያዎች (1 ወርቅ፣ 1 ብር እና 3 ነሐስ) በአጠቃላይ የደረጃ ሰንጠረዡ ላይ 42ኛ በአትሌቲክሱ ብቻ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ ትገኛለች፡፡         

 

 

 

Share