png-logo-white   GREAT ETHIOPIAN RUN

English Arabic Chinese (Simplified) French German Japanese Norwegian Russian Spanish

ታምራት ቶላ በወንዶች 10000 ሜ. ማሬ ዲባባ በሴቶች ማራቶን ሜዳሊያዎቹን አስገኝተዋል


ታምራት ቶላ ነሐስ ያገኘበት የወንዶች 10000ሜ. ፍፃሜ

በሪዮ ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ውድድሮች የሁለተኛ ቀን ውሎ ተጠባቂ ከነበሩት የፍፃሜ ፉክክሮች አንዱ በሆነው የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን አትሌቶች ላለፉት አራት ዓመታት የርቀቱ ንጉስ ሆኖ የቆየውን ትውልደ ሶማሊያዊ የእንግሊዝ አትሌት ሞ ፋራህ ዳግም ማሸነፍ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ሞ ፋራህ በሪዮው ድሉ በኦሊምፒክ ውድድር በተከታታይ ሁለተኛ የ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ድልን በመቀዳጀቱ በታሪክ መዝገብ ላይ ስሙ ከቀደሙት ታላላቅ አትሌቶች ጎራ እንዲመደብ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ እና ኬንያ ተወዳዳሪዎች እርሱን ለማሸነፍ ምን አይነት ታክቲክ ይጠቀሙ ይሆን የሚለው ከውድድሩ በፊት የብዙዎች ጥያቄ የነበረ ቢሆንም በለንደን ኦሊምፒክ እንዲሁም በሞስኮ እና ቤይጂንግ የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ላይ ከተመለከትነው ብዙም የተለየ ነገር ሳይታይ ሞ ፋራህ ዳግም በመጨረሻው ዙር የአጨራረስ ብቃቱ ከተፎካካሪዎቹ ልቆ በመገኘት ለማሸነፍ በቅቷል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ታምራት ቶላ እና ይግረም ደመላሽ እንዲሁም ሶስቱ ኬንያውያን ውድድሩን እየተፈራረቁ በመምራት ለማፍጠን ያደረጓቸው ጥረቶች ስኬታማ መሆን አልቻሉም፡፡ ውድድሩ 15 ዙር እየቀረው የመውደቅ አደጋ አጋጥሞት የነበረው ሞ ፋራህ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስበት በፍጥነት ተነስቶ መቀጠል የቻለ ሲሆን በመጨረሻው ዙር ከኬንያዊው ፖል ታኑዪ ጋር በነበረው ፉክርም 100ሜ. ሲቀር አልፎት በመሄድ በ27 ደቂቃ ከ05.17 ሰከንድ አንደኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ ፖል ታኑዪ በ27፡05.64 ሁለተኛ ኢትዮጵያዊው ታምራት ቶላ በ27፡06.26 ሶስተኛ በመሆን የብር እና የነሐስ ሜዳልያዎችን አሸንፈዋል፡፡ በርቀቱ የዓመቱ ፈጣን ሰዓት ባለቤት የሆነው ኢትዮጵያዊው

ይግረም ደመላሽ በ27፡06.27 አራተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ከአራት ዓመት በፊት በለንደን የብር ሜዳልያ አሸናፊ የነበረው አሜሪካዊው ጋለን ሩፕ በ27፡08.92 አምስተኛ ሆኖ ጨርሷል፡፡ ሌላኛው የኢትዮጵያ ተወካይ አባዲ ሀዲስ (27፡36.34)15ኛ ወጥቷል፡፡

Tamirat Tola finishከለንደን ኦሊምፒክ አንስቶ ያለፉትን አራት ዓመታት የ10000ሜ. ዓለም አቀፍ ክብሮችን ለማንም አላስቀምስ ያለው ሞ ፋራህ ከሪዮ ድሉ በኋላ በሰጠው አስተያየት ‹‹በውድድሩ ላይ በወደቅኩ ግዜ ‹የፈጣሪ ያለህ አበቃልኝ በቃ› ብዬ አስቤ ነበር፡፡ ሆኖም በፍጥነት ተነስቼ

ከተፎካካሪዎቼ ጋር በጥንካሬ መጓዝ ችያለሁ፡፡ ውድድሩ ቀላል አልነበረም ሆኖም ሁሉም ሰው እኔ ምን መስራት እንደምችል ያውቃል፡፡ ስለሰራኋቸው ጠንካራ ስራዎች አስታውሼ በደቂቃ ውስጥ ሁሉ ነገር ፉርሽ ሊሆን እደሚችልም አስቤ ነበር፡፡ ስለዚህ በቀላሉ እጅ ለመስጠት አልፈለግኩም፡፡ በፍጥነት ተነስቼ ስለቤተሰቦቼ አሰብኩ፡፡ ይህን ማሰቤም በጥንካሬ የምቀጥልበት የሆነ ስሜት ፈጥሮልኛል›› ብሏል፡፡ 

ኢትዮጵያዊው የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊ ታምራት ቶላ ሩጫን ከአራት ዓመት በፊት በሰንዳፋ የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ እያለ የጀመረ እና ከአንድ ዓመት በኋላ በኦሮሚያ ክልል ቡድን ውስጥ አልፎ የኦሮሚያ ፖሊስ ክለብን ለመቀላቀል የበቃ፤ ሩጫን ሲጀምርም በቀጥታ ወደጎዳና ላይ ውድድሮች ያመራ ወጣት አትሌት ሲሆን ከሪዮ ኦሊምፒክ የነሐስ ሜዳልያ ድሉ በኋላ በሰጠው አስተያየት ‹‹ሩጫ ስጀምር እሮጥ የነበረው ከ10 ኪ.ሜ. እስከ ማራቶን ባሉት የጎዳና ፉክክሮች ላይ የነበረ ሲሆን ወደአገር አቋራጭ እና ትራክ ውድድሮች የመጣሁትም ካለፈው ዓመት ጀምሮ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በቻይና ጉያንግ የተደረገው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናም ሀገሬን ወክዬ ለመጀመሪያ ግዜ የተወዳደርኩበት ውድድር ነበር›› ካለ በኋላ ስለ ሪዮው ውድድርም ‹‹ሁሉም አትሌት ለማሸነፍ የሚመጣ እንደመሆኑ እኛም የተዘጋጀነውን ያህል ለማሸነፍ ጥረት አድርገናል፡፡ ሆኖም አልተሳካልንም›› ብሏል፡፡ በሪዮ ደ ጃኔይሮ በ10 ሺህ ሜትር የመጀመሪያ የኦሊምፒክ ተሳትፎን አድርጎ ሜዳሊስት ለመሆን የበቃው ታምራት ባለፈው ህዳር ወር የተከናወነው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል 10 ኪ.ሜ. ውድድር አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል፡፡

በሪዮ ከታምራት ጋር በመቶ ሜትር አይነት አጨራረስ ተናንቆ በአራተኛነት ያጠናቀቀው የርቀቱ የዓመቱ ፈጣን ሰዓት ባለቤት ይግረም ደመላሽ ‹‹ውድድሩን በአቅማችን ባሰብነው መልኩ አስኪደነዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ያለንን ሁሉ ሰጥተናል ሆኖም ሞ ፋራህን ልንቆርጠው አልቻልንም፡፡ እንደከዚህ በፊቱም ሳይሆን ተቀራራቢ ፉክክር አድርገን መሸነፋችን ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ›› ያለ ሲሆን ኬንያዊው የብር ሜዳልያ አሸናፊ ፖል ታኑዪ በበኩሉ ‹‹የመጀሪያው አምስት ኪሎ ሜትር የሚፈለገውን ያህል አላፈጠንነውም፡፡ እኔ እና የቡድን ጓደኞቼ እንዲሁም ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ውድድሩን በተሻለ ፍጥነት ብናስኬደው ኖሮ ውጤቱ ከዚህ የተለየ ሊሆን ይችል ነበር›› የሚል አስተያየትን ሰጥቷል፡፡  

 

የእቴነሽ ዲሮ አልበገር ባይነት የተስተዋለበት የሴቶች 3000ሜ. መሰናክል ግማሽ ፍፃሜ

በሪዮ ኦሊምፒክ የሁለተኛ ቀን ውሎ የጠዋት ፕሮግራም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተሳተፉበት የሴቶች 3000ሜ. መሰናክል የግማሽ ፍፃሜ ፉክክር በሶስት ምድብ ተከፍሎ ተካሂዷል፡፡ ከምድብ አንድ ትውልደ ኬንያዊቷ የባሕሬይን ተወዳዳሪ ሩት ጄቤት በ9:12.62 በቀዳሚነት ስታጠናቀቅ ከአራት ዓመት በፊት በለንደን ኦሊምፒክ የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊ የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ ሶፊያ አሰፋ በ9:18.75 ሁለተኛ ወጥታ ለፍፃሜ ማለፏን አረጋግጣለች፡፡ ሶፊያ በለንደን ኦሊምፒክ ያስመዘገብችው የነሐስ ሜዳልያ ባለፈው ዓመት የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ የነበረችው ሩሲያዊቷ ዩሊያ ዛሪፖቫ ውጤቷ በአበረታች መድሀኒት መጠቀም ምክንያት ተሰርዟል መባሉን ተከትሎ ደረጃው ወደብር ሜዳልያ ያድጋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ተግባራዊ አልተደረገም፡፡ 

Etenesh በምድብ ሁለት ኢትዮጵያን ወክላ የተወዳደረችው ሕይወት አያሌው በ9፡35.09 ሰባተኛ ወጥታ ለፍፃሜው ማለፍ ሳትችል ቀርታለች፡፡ ከጉዳት ጋር በተያያዘ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ብዙም የውድድር ተሳትፎ ያልነበራት ሕይወት በሪዮ የግማሽ ፍፃሜ ማጣሪያ ላይም መሰናክሉ ጋር ስትደርስ (በተለይም የውሀው መሰናክል ጋር) የአዘላለል ድክመት በተደጋጋሚ ተስተውሎባታል፡፡ ህይወት የሮጠችበትን ምድብ ኬንያዊቷ ቢአትሪስ ቼፕኮኤች በ9፡17.55 በአንደኛነት ስትጨርስ አሜሪካዊቷ ኤማ ኮበርን (9፡18.12) እና ቱኒዚያዊቷ ሀቢባ ገሪቢ (9፡18.71) በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተው ለፍፃሜ ተወዳዳሪነት በቅተዋል፡፡

የሶስተኛው ምድብ የግማሽ ፍፃሜ ፉክክር የኢትዮጵያዊቷ አትሌት እቴኔሽ ዲሮ አልበገር ባይነት የዕለቱን የስታድየም ታዳሚዎች እና በስፍራው የነበሩ ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ሚድያዎችን ትኩረት የሳበበት ነበር፡፡ ከተጀመረ አንስቶ ከኬንያዊቷ ሄይቪን ኪገን ጄፕኬሞይ ጋር የውድድሩ ፊት መሪ ሆና የቆየችው እቴነሽ ሊጠናቀቅ ሶስት ዙር ሲቀረው ከኋላ የቀኝ እግር ጫማዋ ተረግጦ በመውለቁ እሱን ለማስተካከል ስትቆም ከኋላዋ ከሚሮጡ ሁለት አትሌቶች ጋር ተጋጭታለች፡፡ እቴነሽ ጫማዋን መልሳ ለማድረግ ስትሞክር ተፎካከሪዎቿ ጥለዋት በመሄዳቸውም መጀመሪያ ጫማዋን ቀጥላም ካልሲዋን በማውለቅ ወርውራ በአንድ ባዶ እግር ተፎካከሪዎቿ ላይ ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች፡፡ ጥረቷ ሳይሳካ ሰባተኛ ሆና ለማጠናቀቅ ብትገደድም የቀኝ እግር ጫማዋን አውልቃ ጥለዋት የሄዱት ተፎካካሪዎቿ ላይ ለመድረስ ስትሞክር የስታድየሙ ታዳሚ በሙሉ በከፍተኛ ድምፅ ድጋፉን ሲሰጣት ነበር፡፡ ሆኖም ሳይሳካላት ሰባተኛ ሆና ለማጠናቀቅ ተገዳለች፡፡ እቴነሽ ውድድሩ ካለቀ በኋላ በውጤቷ መበላሸት አዝና የመሮጫ ትራኩ ላይ ቁጭ ብላ ስታነባም ታይታለች፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማሕበር ከውድድሩ በኋላ በቀረበለት የይግባኝ ጥያቄ መሰረት የእቴነሽን የአልበገር ባይነት ጥረትም ከግምት ውስጥ አስገብቶ እርሷ እና በተፈጠረው ክስተት ተጋጭተው የወደቁትን ሁለት አትሌቶች (አየርላንዳዊቷ ሳራ ትሬሲ እና ጃማይካዊቷ አይሻ ፕራውት) ለፍፃሜው ውድድር እንዲያልፉ አድርጓል፡፡ እቴነሽ በ2016 ዓመተ ምህረት በሴቶች 3000ሜ. መሰናክል በተደረጉ ውድድሮች ከሩት ጄቤት፣ ኤማ ኮበርን እና ሄይቪን ኪገን ቀጥላ አራተኛውን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበች አትሌት ስትሆን ምንም እንኳ በርቀቱ እንድትወዳደር ባይደረግም በ5000 ሜትርም ዘንድሮ ከኢትዮጵያ ሶስተኛውን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ የቻለች አትሌት ናት፡፡                   

 

የመካከለኛ ርቀት ግማሽ ፍፃሜዎች

በመካከለኛ ርቀት የግማሽ ፍፃሜ ፉክክሮች መሐመድ አማን ሲወድቅ በሴቶች 1500ሜ. ላይ የተሳተፉት ሶስቱም አትሌቶች ለፍፃሜው አልፈዋል፡፡ በሁለተኛው ቀን ምሽት ላይ በተካሔደው የወንዶች 800ሜ. ግማሽ ፍፃሜ በሁለተኛ ምድብ የተወዳደረው መሐመድ አማን ከምድቡ የመጨረሻውን (8ኛ) ደረጃ ይዞ በጨረስ ሳያልፍ የቀረ ሲሆን ዴቪድ ሩዲሻን ጨምሮ ሌሎቹ ተጠባቂ አትሌቶች ለፍፃሜው በቅተዋል፡፡ 

በሶስተኛው ቀን ምሽት ላይ በተካሄደው የሴቶች 1500ሜ. ግማሽ ፍፃሜ ላይ የተሳተፉት በምድብ አንድ ዳዊት ስዩም እና በሱ ሳዶ እንዲሁም በምድብ ሁለት ገንዘቤ ዲባባ በቀጥታ የፍፃሜ ተፋላሚ መሆናቸውን ያረጋገጡበትን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕዬጎን በ4፡03.95 ቀዳሚ ሆና ከጨረሰችበት ምደብ አንድ ዳዊት ስዩም በ4:04.23 ሁለተኛ በሱ ሳዶ በ4:05.19 አራተኛ ሆነው ለፍፃሜው ሲያልፉ ምድብ ሁለትን በ4:03.06 በቀዳሚነት የጨረሰችው ገንዘቤም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ ለሊት 10፡30 ላይ ለሚካሄደው የፍፃሜ ፉክክር በቅታለች፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በለንደን የ1500ሜ. የማጣሪያ ውድድር ላይ እየተሳተፈች እያለ ጉዳት ገጥሟት ለማቋረጥ ተገዳ የነበረችው ገንዘቤ ‹‹በፍፃሜው ብዙ አትሌቶች እኔን ለመቅደም ተዘጋጅተው የሚመጡ መሆኑ አይቀርም፡፡ እኔም ግን የራሴን ታክቲክ በመጠቀም ሜዳልያ ለማሸነፍ እሞክራለሁ፡፡›› ብላለች፡፡

ማሬ ዲባባ የነሐስ ሜዳያ ያስገኘችበት የሴቶች ማራቶን

በሶስተኛው ቀን ጠዋት ፕሮግራም የተያዘለት የሴቶች ማራቶን ውድድር ከቀደሙት ሁለት ቀናት ለየት ባለ ሞቃት የአየር ሁኔታ ታጅቦ የተከናወነ ሲሆን ኬንያዊቷ ጀሚማ ጄላጋት ሰምጎንግ ለሀገሯ የመጀመሪያውን የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ድል ያስመዘገበችበት፣ በትውልድ ኬንያዊ በዜግነት ባሕሬናዊ የሆነችው ኢዩንስ ጄፐኪሩዪ ኪራዋ የብር ኢትዮጵያዊቷ ማሬ ዲባባ የነሐስ ሜዳልያ ድል የተቀዳጁበት ሆኖ ተጠናቋል፡፡ 

Women MArathonኢትዮጵያዊቷ ትግስት ቱፋ 17.8 ኪሎ ሜትር ከሮጠች በኋላ የቀኝ እግሯ ላይ በተፈጠረ ችግር ለማቋረጥ እስከተገደደችበት አጋጣሚ ድረስ ከቡድን ጓደኞቿ ትርፊ እና ማሬ ጋር ከፊት መሪዎቹ ተርታ ብርቱ ተፎካካሪ ሆነው የቆዩ ሲሆን ትርፊ እና ማሬ እስከመጨረሻው በፉክክሩ ውስጥ ከቆዩት ሰባት አትሌቶች መካከልም ነበሩ፡፡ ከ35ኛው ኪሎ ሜትር በኋላ የባህሬይኗ ኪራዋ ወደፊት ተነገጥላ ስትወጣ ማሬ እና ሰምጎንግ የተከተሏት ሲሆን በመጨረሻም አብዛኛውን ሰዓት ውድድሩ ላይ አድፍጣ ስትከተል የቆየችው ሰምጎንግ ከ40ኛው ኪሎ ሜትር በኋላ የቆጠበችውን አቅም ተጠቅማ በ2፡24፡04 ቀዳሚ ሆና ጨርሳለች፡፡ ባለፈው ዓመት በቤይጂንግ የዓለም ሻምፒዮና ማሬን ተከትላ የብር ሜዳልያ አግኝታ የነበረችው ኪራዋ በ2፡24፡13 ሁለተኛ በመውጣት በኦሊምፒክ ውድድርም የብር ሜዳልያን ስታገኝ ከአራት ዓመት በፊት በለንደን ኦሊምፒክ የማራቶን ተሳትፎዋ 23ኛ ሆና ማጠናቀቋ የሚታወሰው ማሬ በ2፡24፡30 የነሐስ ሜዳልያ ባለቤት ሆናለች፡፡ ትርፊ ፀጋዬም በጥሩ አቋም በ2:24:47 አራተኛ ሆና ጨርሳለች፡፡

የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊዋ ማሬ ከድሏ በኋላ ‹‹ውድድሩ ትንሽ ሙቀት እና ንፋስ የነበረው ቢሆንም መጥፎ የሚባል አልነበረም፡፡ እኔ ከ25ኛው ኪሎ ሜትር በኋላ ውጋት ይዞኝ እየታገልኩ የነበረ ሲሆን አርባኛው ኪሎ ሜትር ላይ ስደርስ መቋቋም አቅቶኝ ተፎካካሪዎቼን ለመልቀቅ ተገድጃለሁ›› ያለች ሲሆን ‹‹ትግስት እስክትወጣ ሶስታችንም ከወጣች በኋላም ከትርፊ ጋር እየተነጋገርን እየተጋገዝን ጥሩ ስንጓዝ ነበር፡፡ በሜዳልያ ደረጃ ውስጥ ገብቼ እንደማጠናቅቅ አስብ ነበር፡፡ ፈጣሪ ምስጋና ይድረሰው ያሰብኩትን አሳክቻለሁ›› በማለትም አክላለች፡፡ በማራቶን ውድድሩ መጠናቀቂያ አካባቢ ብራዚላዊ የፖለቲካ ተቃዋሚ ተቃውሞውን ለመግለፅ በአትሌቶቹ የመሮጫ መስመር ላይ ገብቶ የነበረ ቢሆንም የተወዳዳሪዎቹን ጉዞ ሳያስተጓጉል በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል፡፡ 

የሁለቱም ፆታዎች የ100ሜ. ፍፃሜ እና የቫን ኔይከርክ የ400ሜ. የዓለም ሪኮርድ

ከኦሊምፒክ የመም (የትራክ) ላይ ውድድሮች ከፍተኛ የተመልካች መስህብ በመሆን የሚታወቁት የሁለቱም ፆታዎች የ100ሜ. የፍፃሜ ፉክክሮች ትላንት እና ከትላንት በስቲያ የተከናወኑ ሲሆን የሁለተኛው ቀን ውድድሮች መዝጊያ በነበረው የሴቶቹ ፉክክር ጃማይካዊቷ ቶምፕሰን ኤላኔ በ10.71 ሰከንድ ቀዳሚ ሆና አዲሷ የኦሊምፒክ ሻምፒዮን ስትሆን አሜሪካዊቷ ቦዊ ቶሪ (10.83) እና ጃማይካዊቷ ሼሊ-አን ፍሬዘር (10.86) በቅደም ተከተል የብር እና ነሐስ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ 

የሶስተኛው ቀን መዝጊያ እና ሰሞኑን በተመልካች ድርቅ ለተመታው ስታድየም መሙላት ምክንያት በነበረው የወንዶች 100ሜ. ፍፃሜ ጃማይካዊው ዩሴይን ቦልት በርቀቱ የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳልያ ሀት-ትሪክ (ቤይጂንግ 2008፣ ለንደን 2012 እና ሪዮ 2016) የሰራበትን ድል አስመዝግቧል፡፡ ቦልት በ9.81 ሰከንድ አንደኛ በወጣበት ውድድር አሜሪካዊው ጀስቲን ጋትሊን በ9.84 ሰከንድ አንዲሁም ካናዳዊው አንድሬ ደ ግራሰ በ9.91 ሰከንድ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ወጥተው የብር እና ነሐስ ሜዳልያ አሸናፊ ሆነዋል፡፡ 

በሶስተኛው ቀን ከተከናወኑት የፍፃሜ ውድድሮች መካከል አንዱ በሆነው የወንዶች 400ሜ. ደቡብ አፍሪካዊው ዋይዴ ቫን ኔይከርክ 43.03 ሰከንድ በሆነ ሰዓት ላለፉት 17 ዓመታት በአሜሪካዊው ማይክል ጆንሰን ተይዞ የቆየውን የዓለም ሪኮርድ በ15 ሰከንድ በማሻሻል ጭምር የወርቅ ሜዳልያን አሸንፏል፡፡ ግራናዳዊው ጀምስ ኪራኒ (43.76) እና አሜሪካዊው ላሽዋን ሜሪት (43.85) ብርና ነሐስ ሜዳልያ ወስደዋል፡፡           

Share

ተጨማሪ ዜናዎች

በሪዮ ደ ጃኔይሮ በመካከለኛ ርቀት የመጀመሪያውን የኦሊምፒክ ሜዳልያ እንደምናስመዘግብ ይጠበቃል

የማራቶን እና 3000ሜ. መሰናክል የሜዳልያ ድሎቻችን ይቀጥሉ ይሆን?
ቀጣዩ ዘገባ በሪዮ ኦሊምፒክ በመካከለኛ ርቀት፣ በ3000ሜ. መሰናክል እና በማራቶን በሁለቱም ፆታዎች እንዲሁም በ20 ኪ.ሜ. እርምጃ ሴቶች የኢትዮጵያ ተወካዮች በሆኑት አትሌቶች ዙሪያ የተወሰነ ግንዛቤን ለማስጨበጥ ይሞክራል፡፡                  

መካከለኛ ርቀት
በመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በነበሯት የኦሊምፒክ ተሳትፎዎች ምንም አይነት ሜዳልያን ያላስመዘገበችበት ቢሆንም በሪዮ ኦሊምፒክ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው የመካከለኛ ርቀት የሜዳልያ ድል ሊመዘገብ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
በወንዶች 800 ሜ. ከአራት ዓመት በኋላም ዳግም ብቸኛው የኢትዮጵያ ተወካይ ሆኖ ለመቅረብ የበቃው መሐመድ አማን ከለንደን ኦሊምፒክ በኋላ በ2013 ሞስኮ ላይ የዓለም ሻምፒዮን፣ በ2014 ሶፖት ላይ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮን አንዲሁም በሞሮኮ ማራካሽ በተካሄደው የ2014 ኮንቲኔንታል ካፕ የብር ሜዳልያ አሸናፊ ቢሆንም የ2015 እና 2016 ውድድር ዓመቶች የውድድር ተሳትፎው ተደጋጋሚ የአቋም መዋዠቆች የታየበት ነበር፡፡ ሌሎች ሁለት አትሌቶችን ማሳተፍ ይቻል የነበረ ቢሆንም በርቀቱ ለመሳተፍ የሚያስችለውን ሰዓት የሚያሟሉ ሌሎች አትሌቶችን ማፍራት አለመቻሉ አሁንም ትልቅ ክፍተት ሆኖ መቀጠሉን ያመላክታል፡፡

Read more...

የሪዮ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ ተሳትፎ ከባርሴሎና 92 ወዲህ ዝቅተኛው የወርቅ ሜዳልያ ቁጥር የተመዘገበበት ሆኖ ተጠናቀቀ

አልማዝ የጥሩነሽን የለንደን ገድል ስትደግም ገንዘቤ በመካከለኛ ርቀት ፈይሳ በማራቶን የመጀመሪያ የሆኑ ሜዳልያዎችን አስገኝተዋል   

በሪዮ ኦሊምፒክ ከነሐሴ 6 ጀምሮ በጆአኦ ሀቫላንጅ ኦሊምፒክ ስታዲየም መም እንዲሁም በጎዳና ላይ ሲካሄዱ የሰነበቱት የአትሌቲክስ ፉክክሮች ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ ዳግም ወደኦሊምፒክ ተሳትፎ ከተመለሰችበት የ1992ቱ የባርሴሎና ኦሊምፒክ ወዲህ ዝቅተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ቁጥር በማስመዝገብ አጠናቃለች፡፡  


Read more...

ገንዘቤ ዲባባ በሪዮ ኦሊምፒክ የሴቶች 1500ሜ. የብር ሜዳልያ አስገኘች ፤ በኢትዮጵያ የ60 ዓመት የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በመካከለኛ ርቀት የተገኘ የመጀመሪያው ሜዳልያ

ብራዚሏ ሪዮ ደ ጃኔይሮ ከተማ አስተናጋጅነት እየተከናወነ ባለው 31ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የአትሌቲክስ ፉክክር አምስተኛ ቀን ውሎ ከተከነናወኑት የፍፃሜ ውድድሮች አንዱ የሴቶች 1500ሜ. ሲሆን ገንዘቤ ዲባባ በኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕዬጎን ተቀድማ የብር ሜዳልያ ባለቤት ሆናለች፡፡ በንፅፅር በማጣሪያው ላይ ከተመዘገበው በዘገየ ሰዓት በተጠናቀቀው የፍፃሜ ፉክክር የመጀመሪያው ዙር ቀርፋፋ የነበረ ሲሆን ገንዘቤም ይህን ዙር ከተፎካካሪዎቿ በስተኋላ ሆና ስትከተል ቆይታለች፡፡ በቅድመ ውድድር ዕቅዷ የመጨረሻ ሩጫዋን ስድስት መቶ ሜትር ላይ ልትጀምር አስባ እንደገባች የጠቀሰችው ገንዘቤ ከብር ሜዳልያ ድሏ በኋላ ‹‹በውድድሩ ላይ ቦታ ለመያዝ በነበረው ፉክክር የመጨረሻ ሩጫዬን ቀደም ብዬ 700ሜ. እየቀረኝ ለመጀመር ተገድጃለሁ፡፡ በጉዳት ምክንያት ብዙ ዝግጅት ማድረግ አልቻልኩም እንደዛም ሆኖ ለሀገሬ ብር ሜዳልያ ማምጣት ችያለሁ›› ያለች ሲሆን አሰልጣኟ ጀማ አደን ከአበረታች መድኃኒት ጋር በተያያዘ መጠርጠሩ በእርሷ ላይ ስለፈጠረው ተፅኖ ስታወራም ‹‹በጀማ ጉዳይ በተለይ በሀገራችን ሚዲያዎች ስሜ ሲነሳ ነበር፡፡ ጀማ ተጠረጠረ ማለት እኔ ተያዝኩ ወይም ተጠረጠርኩ ማለት አይደለም፡፡ እኔን ከጀማ ጋር የሚያገናኘኝ ስራ ነው እንጂ ስለዚህ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ይህ ጉዳይ በሀገራችን ሚዲያዎች ትንሽ ጫና አሳድሮብኛል›› ብላለች፡፡ ገንዘቤ በሪዮ ኦሊምፒክ ያሳካችው የብር ሜዳልያ ድል በኢትዮጵያ የ60 ዓመት የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በመካከለኛ ርቀት የተገኘ የመጀመሪያው ሜዳልያ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የኢትዮጵያ የእስከዛሬ የሜዳልያ ድሎች በሁለቱም ፆዎች በ50000ሜ.፣ 10000ሜ.፣ ማራቶን እና 3000ሜ. መሰናክል የተገኙ የነበሩ ሲሆን ገንዘቤ በሪዮ ደ ጃኔይሮ ያመጣችው የ1500ሜ. የብር ሜዳልያ ስኬት የተመዘገበባቸውን የውድድር አይነቶች ቁጥር በአንድ ከፍ ያደረገም ነው፡፡

Read more...