png-logo-white   GREAT ETHIOPIAN RUN

English Arabic Chinese (Simplified) French German Japanese Norwegian Russian Spanish

የሪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ፉክክር ከተጀመረ ከስምንት ቀን በኋላ (ሐምሌ 6/2008) መካሄድ በጀመረው የአትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አልማዝ አያና በሴቶች 10 ሺህ ሜትር የርቀቱን የዓለም ሪኮርድ በመስበር ጭምር በአትሌቲክስ የመጀመሪያዋ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤት ለመሆን በቅታለች፡፡ ከዚህ በፊት በርቀቱ የቤይጂንግ እና ለንደን ኦሊምፒኮች የወርቅ ሜዳልያ ባለቤት የነበረችው ጥሩነሽ ዲባባም በአራተኛ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ከአልማዝ አያና እና ኬንያዊቷ ቪቪያን ቼሪዮት ቀጥላ በሶስተኛነት በማጠናቀቅ የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊ ሆናለች፡፡

ተጀምሮ እስኪያልቅ ኬንያዊቷ የአፍሪካ ሻምፒዮን አሊስ አፕሮት እና አልማዝ አያና ተቀባብለው የመሩበት ሴቶች 10 ሺህ ሜ. ፉክክር ከተጀመረ ከሶስተኛው ዙር አንስቶ በሁለቱ ፊት መሪዎች አስገዳጅነት ስምንት አትሌቶች - አፕሮት (ኬንያ)፣ አልማዝ (ኢትዮጵያ)፣ ቼሪዮት (ኬንያ)፣ ያስሚን ካን (ቱርክ)፣ ጥሩነሽ (ኢትዮጵያ)፣ ቤትሲ (ኬንያ)፣ ገለቴ (ኢትዮጵያ) እና ሀድል (ዩ.ኤስ.ኤ) - በቅደም ተከተል ተነጥለው የወጡበት የነበረ ሲሆን 4800ሜ. ላይ ሲደርሱ ገለቴ እና ሞሊ ሀድል ወደኋላ ቀርተዋል፡፡ 5200ሜ. ከሸፈኑ በኋላ ውድድሩን የመምራቱን ኃላፊነት የተረከበችው አልማዝ ፍጥነቷን በመጨመር ስትወጣ ኬንያዊቷ ቼሪዮት የተከተላቻት ቢሆንም በቀጣዮቹ ዙሮች እየጨመረ የመጣውን የአልማዝ ፍጥነት መቋቋም ሳትችል ቀርታ ተሸንፋለች፡፡ በአልማዝ እና ቼሪዮት መካከል የነበረው ልዩነት በመጨረሻዎቹ ስምንት ዙሮች እየሰፋ ሄዶ አልማዝ 29 ደቂቃ ከ17.45 ሰከንድ በሆነ አዲስ የዓለም እና የኦሊምፒክ ሪኮርድ ሰዓት በሪዮ ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ውድድር የመጀመሪያዋ የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ ለመሆን በቅታለች፡፡ ከውድድሩ ጥቂት ወራት ቀደም ብላ በሰጠችው አስተያየት አልማዝንም ቢሆን እንደማትፈራ ተናግራ የነበረችው ኬንያዊቷ ቼሪዮት በዘጠና ሜትር ያህል ልዩነት ተቀድማ የራሷ ምርጥ እና የኬንያ ሪኮርድ በሆነ 29:32.53 ሰዓት ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች፡፡ 

ለወርቅ ሜዳልያ አሸናፊነት በኢትዮጵያዊቷ አልማዝ እና በኬንያዊቷ ቼሪዮት መካከል ይደረግ የነበረው ትንቅንቅ ስምንት ዙር እየቀረው በአልማዝ ፍፁም የበላይነት ሲቀጥል ከበስተኋላ በሌሎች ሁለት የኢትዮጵያ እና ኬንያ አትሌቶች (ጥሩነሽ ዲባባ እና አሊስ አፕሮት) መካከል የተመልካችን ቀልብ የሚስብ የነሐስ ሜዳልያ ፉክክር እየተደረገ ነበር፡፡ ውድድሩ ሊጠናቀቅ ስድስት ዙር ሲቀረው ጥሩነሽ ከበስተኋላ በመምጣት በመካከላቸው የነበረውን ልዩነት አጥብባ አፕሮትን ለማለፍ ሞክራ የነበረ ቢሆንም ብዙም ሳይጓዙ አፕሮት መልሳ የሶስተኝነቱን ደረጃ ለመያዝ ችላለች፡፡ ከዛ በኋላ በቀሩት አራት ዙሮች ጥሩነሽ ኬንያዊቷ አፕሮትን በቅርብ እርቀት ስትከተላት ቆይታ 400ሜ. ሲቀራቸው ለወትሮው በሚታወቀው የመጨረሻ ዙር ፈጣን አሯሯጧ ጥላት በመሄድ የሯሷ ምርጥ በሆነ 29:42.56 ሰዓት ለኢትዮጵያ የነሐስ ሜዳልያን ለማስገኘት በቅታለች፡፡ 

በቻይናዊቷ ዋንግ ጁኒሲያ እ.አ.አ. በ1993 ዓ.ም ተመዝግቦ 23 ዓመት ሊደፍን የተቃረበውን 29:31.78 የነበረ የዓለም ሪኮርድ እና በቤጂንግ ኦሊምፒክ በጥሩነሽ ዲባባ የተመዘገበውን 29:54.66  የነበረ የኦሊምፒክ ሪኮርድ ደርባ የሰባበረችው አልማዝ አያና ከድሏ በኋላ በሰጠችን አስተያየት ‹‹ውድድሩ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ከእነ ጥሩዬ እና ቪቪያን ጋር ሮጬ በማሸነፌ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ እኔ የሰራሁት በጣም ትንሽ ነው፡፡ ይህን ተዓምር እንዳሳካ የረዳኝ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፡፡ ሪኮርድ የመስበር ዕቅዱ ያልነበረኝ ሲሆን ጥረቴ ውድድሩን ለማሸነፍ ብቻ ነበር፡፡ ሆኖም እግዚአብሔር ያላሰብኩትን ስኬት ደራርቦ ሰጥተቶኛል›› ያለች ሲሆን ‹‹ኬንያዊቷ አሊስ አፕሮት ከመጀመሪያው አንስቶ ውድድሩን በማፍጠን እኛን ለመቁረጥ ብታስብና ብትሞክርም የእርሷ ከፊት በፍጥነት መሮጥ ለእኔ በጣም ጥሩ ሆኖልኛል፡፡ ውድድሩ እንዲሆን በምፈልገው መንገድ እንዲሄድ በማድረግም ጥሩ አሯሯጭ ሆናልኛለች፡፡ የአየር ሁኔታው ትንሽ ቀዝቃዛ የነበረ መሆኑ እንደልብ ባያስኬደኝም ባጠቃላይ ውድድሩ ለእኔ ዕቅድ የተመቸ ነበር›› በማለትም አክላለች፡፡ አልማዝ የዛሬው ውድድር ከአራት ቀን በኋላ የማጣሪያ ፉክክር በምታደርግበት የ5000ሜ. ውድድሯ ላይ የድካም ተፅዕኖ ይፈጥርብኛል ብለሽ አትሰጊም በሚል ለቀረበላት ጥያቄ ምላሽ ስትሰጥም ‹‹እንዳይበላሽብኝ እፈራ የነበረው እንዲያውም የ10 ሺህ ሜትር ውድድርን ነበር፡፡ የዛሬው ውድድር በቀጣይ በማደርገው የ5000ሜ. ፉክክር ላይ ምንም አይነት ተፅዕኖ ይኖረዋል ብዬ አልሰጋም›› ብላለች፡፡ 

  

10000 medalia

‹ለልጄ ስል የሜዳልያ ደረጃ ውስጥ ገብቼ መመለስ እንዳለብኝ አስብ ነበር›› ጥሩነሽ ዲባባ

አልማዝ አያና የዓለም ሪኮርድ በመስበር ጭምር የወርቅ ሜዳልያውን በማሸነፏ የተሰማትን ደስታ በማስቀደም አስተያየቷን መስጠት የጀመረችው የሪዮ ኦሊምፒክ የሴቶች 10 ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊዋ ጥሩነሽ ዲባባ ‹‹ወልጄ ከተነሳሁ በኋላ ወደውድድር የተመለስኩት በቅርቡ ነው፡፡ ለሪዮ ዝግጅት ልምምድ ለመስራት ልጄን ትቼ ስወጣ በጣም ነበር የሚሰማኝ፡፡ ስለለፋሁ እና ስለደከምኩ ደግሞ የግድ ለእርሱ ሜዳልያ ውስጥ ገብቼ የሆነ ነገር ይዤለት እንደምመለስ ነበር የማስበው›› ያለች ሲሆን ‹‹ውድድሩ ደማቅ እና ደስ የሚል ነበር፡፡ ሶስተኛ በመውጣቴም በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ የአየር ሁኔታው ከአዲስ አበባ ጋር የሚመሳሰል ስለሆነ ምንም የሚከብድ ነገር አልነበረውም፡፡ የዝግጅት ግዜዬ አጭር የነበረ በመሆኑ የውድድሩን ከመጀመሪያው መፍጠን መቋቋም አልቻልኩም፡፡ የዚህ አይነቱን ፍጥነት ለቋቋም ብዙ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለሶስተኛነቱ ከኬንያዊቷ አትሌት ጋር በነበረው ፉክክር አራት ዙር እየቀረ አልፌያት ለመሄድ ሞክሬ በድጋሚ ከኋላ መከተሉን የመረጥኩት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያለችው አትሌት ላይ መድረስ እንደማልችል ስለገባኝ እና ለመጨረሻው ፉክክር አቅሜን ለመቆጠብ ስለፈለግኩ ነበር›› በማለትም አክላለች፡፡ የዓለም ሪኮርድ በኦሊምፒክ ውድድር ላይ መሰበሩን አስመልክቶ ስትናገርም ‹‹የዓለም ሪኮርድ መሰበሩ እና እኔ እራሴ ብዙም ዝግጅት ሳላደርግ የራሴን ምርጥ ሰዓት ለማሻሻል መብቃቴ በጣም ያልጠበቅኩትና ያስገረመኝ እንዲሁም ያስደሰተኝ ነገር ነው፡፡ በ10 ሺህ ሜትር ሪኮርድ የመስበር ሙከራን አድርጌ የማላውቅ ሲሆን የራሴን ምርጥ ሰዓት ያስመዘገብኩትም በቤይጂንግ ኦሊምፒክ ላይ ነበር›› ብላለች፡፡   

በሪዮ ደ ጃኔይሮ አራተኛ የኦሊምፒክ ተሳትፎን በማድረግ በኢትዮጵያ የብዙ ግዜ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ሪኮርድ ያስመዘገበችው ጥሩነሽ ዲባባ የሴቶች 10000ሜ. ፉክክር በ1988 ዓ.ም. የኦሊምፒክ ስፖርት ሆኖ መካሄድ ከጀመረበት ግዜ አንስቶ እስካሁን ባለው ሂደት ከተካሄዱት ስምንት ውድድሮች ኢትዮጵያ የአምስቱን ወርቅ ሜዳልያዎች እንድታሸንፍ እና የበላይነቱን እንድትይዝ ከአክስቷ ደራርቱ ቱሉ እኩል ሁለት ግዜ በማሸነፍ የበኩሏን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተች ድንቅ አትሌት ናት፡፡ የሪዮው የሴቶች 10 ሺህ ሜትር ፍፃሜ 1 የዓለም፣ 1 የኦሊምፒክ፣ 1 የአካባቢ እና 8 ብሔራዊ ሪኮርዶች የተሻሻሉበት እንዲሁም 18 የግል ምርጥ ሰዓቶች የተመዘገቡበት ሆኖ ተጠናቋል፡፡  

በአትሌቲክሱ የመጀመሪያ ቀን ውሎ ከሴቶች 10 ሺህ ሜትር ፍፃሜ በፊት በ12 ምድብ ተከፍሎ  በተከናወነው የወንዶች 800ሜ. የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ በሰባተኛው ምድብ ተደልድሎ የነበረው ኢትዮጵያዊው መሐመድ አማን በ1፡48.33 ፈረንሳዊውን ፒዬር አምብሮስ ቦሰ (1፡48.12) ተከትሎ ሁለተኛ በመውጣት ለተከታዩ ማጣሪያ አልፏል፡፡ መሐመድ ከውድድሩ በኋላ በሰጠን አጭር አስተያየት ‹‹እንደመጀመሪያ ማጣሪያ ውጤቱ ጥሩ ነው›› ብሏል፡፡ በወንዶች 800ሜ. ማጣሪያ ኬንያውኑ ዴቪድ ሩዲሻ እና ፈርጉሰን ሮቲች፣ ፖላንዳዊው ማርሲን ሌቫንዶቭስኪ እና ቦስኒያዊው አመል ቱካን ጨምሮ አብዛኞቹ ተጠባቂ አትሌቶች ወደተከታዩ ዙር ሲያልፉ የለንደን ኦሊምፒክ የርቀቱ የብር ሜዳልያ ባለቤት የሆነው ቦትስዋናዊው ኒጄል አሞስ አልጄሪያዊው ቶፊቅ ማክሉፊ ቀዳሚ ሆኖ ከጨረሰበት አምስተኛ ምድብ ሰባተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ለተከታዩ ዙር ሳያልፍ መቅረቱ ብዙዎችን ያስገረመ ክስተት ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በምሽቱ ፕሮግራም ላይ በተካሄደው የሴቶች 1500ሜ. የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ላይም ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን በምድብ አንድ የሮጠችው ገንዘቤ ዲባባ በ4:10.61 እና በምድብ ሶስት የተፎካከረችው ዳዊት ስዩም በ4፡05.33 ሁለቱም የምድባቸው ቀዳሚ በመሆን በምድብ ሁለት የሮጠችው በሱ ሳዶ በ4፡08.11 ስድስተኛ በመውጣት ሁሉም ወደተከታዩ ዙር አልፈዋል፡፡ ገንዘቤ ዲባባ ከመጀመሪያ የማጣሪያ ውድድሯ በኋላ በሰጠችው አስተያየት ‹‹የመጀመሪያ ማጣሪያ እንደመሆኑ ውጤቴ ጥሩ ነው፡፡ በመሀል ወደመጀመሪያው መስመር ገብቼ የመጠለፍ አደጋ ሊገጥመኝ የነበረ ቢሆንም ምንም ሳልሆን ወጥቻለሁ፡፡ ብቻዬን ከፊት እየመራሁ በነበረበት ሁኔታ መቶ ሜትር ያህል ሲቀረኝ እንደመቆም ያልኩት ስክሪን እያየሁ እየሮጥኩ ስለነበር የሜዳውን ጠርዝ የነካሁ መስሎኝ ነበር›› ስትል ሶስተኛውን ምድብ በአሸናፊነት የጨረሰችው ዳዊት ስዩም በበኩሏ ‹‹የመጀመሪያ የኦሊምፒክ ተሳትፎዬ እንደመሆኑ የማጣሪያውን ውድድር በቀዳሚነት መጨረሴ ጥሩ ነገር ነው፡፡ ቀጣይ ውድድሮችን ከፈጣሪ ጋር እንደአመጣጣቸው የማያቸው ይሆናል›› ብላለች፡፡    

 

Share

ተጨማሪ ዜናዎች

በሪዮ ኦሊምፒክ የአትሌቲክሱ የሁለተኛ እና ሶስተኛ ቀን ውሎዎች ኢትዮጵያ ተጨማሪ ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎችን አግኝታለች

ታምራት ቶላ በወንዶች 10000 ሜ. ማሬ ዲባባ በሴቶች ማራቶን ሜዳሊያዎቹን አስገኝተዋል


ታምራት ቶላ ነሐስ ያገኘበት የወንዶች 10000ሜ. ፍፃሜ

በሪዮ ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ውድድሮች የሁለተኛ ቀን ውሎ ተጠባቂ ከነበሩት የፍፃሜ ፉክክሮች አንዱ በሆነው የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን አትሌቶች ላለፉት አራት ዓመታት የርቀቱ ንጉስ ሆኖ የቆየውን ትውልደ ሶማሊያዊ የእንግሊዝ አትሌት ሞ ፋራህ ዳግም ማሸነፍ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ሞ ፋራህ በሪዮው ድሉ በኦሊምፒክ ውድድር በተከታታይ ሁለተኛ የ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ድልን በመቀዳጀቱ በታሪክ መዝገብ ላይ ስሙ ከቀደሙት ታላላቅ አትሌቶች ጎራ እንዲመደብ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ እና ኬንያ ተወዳዳሪዎች እርሱን ለማሸነፍ ምን አይነት ታክቲክ ይጠቀሙ ይሆን የሚለው ከውድድሩ በፊት የብዙዎች ጥያቄ የነበረ ቢሆንም በለንደን ኦሊምፒክ እንዲሁም በሞስኮ እና ቤይጂንግ የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ላይ ከተመለከትነው ብዙም የተለየ ነገር ሳይታይ ሞ ፋራህ ዳግም በመጨረሻው ዙር የአጨራረስ ብቃቱ ከተፎካካሪዎቹ ልቆ በመገኘት ለማሸነፍ በቅቷል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ታምራት ቶላ እና ይግረም ደመላሽ እንዲሁም ሶስቱ ኬንያውያን ውድድሩን እየተፈራረቁ በመምራት ለማፍጠን ያደረጓቸው ጥረቶች ስኬታማ መሆን አልቻሉም፡፡ ውድድሩ 15 ዙር እየቀረው የመውደቅ አደጋ አጋጥሞት የነበረው ሞ ፋራህ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስበት በፍጥነት ተነስቶ መቀጠል የቻለ ሲሆን በመጨረሻው ዙር ከኬንያዊው ፖል ታኑዪ ጋር በነበረው ፉክርም 100ሜ. ሲቀር አልፎት በመሄድ በ27 ደቂቃ ከ05.17 ሰከንድ አንደኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ ፖል ታኑዪ በ27፡05.64 ሁለተኛ ኢትዮጵያዊው ታምራት ቶላ በ27፡06.26 ሶስተኛ በመሆን የብር እና የነሐስ ሜዳልያዎችን አሸንፈዋል፡፡ በርቀቱ የዓመቱ ፈጣን ሰዓት ባለቤት የሆነው ኢትዮጵያዊው

Read more...

ገንዘቤ ዲባባ በሪዮ ኦሊምፒክ የሴቶች 1500ሜ. የብር ሜዳልያ አስገኘች ፤ በኢትዮጵያ የ60 ዓመት የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በመካከለኛ ርቀት የተገኘ የመጀመሪያው ሜዳልያ

ብራዚሏ ሪዮ ደ ጃኔይሮ ከተማ አስተናጋጅነት እየተከናወነ ባለው 31ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የአትሌቲክስ ፉክክር አምስተኛ ቀን ውሎ ከተከነናወኑት የፍፃሜ ውድድሮች አንዱ የሴቶች 1500ሜ. ሲሆን ገንዘቤ ዲባባ በኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕዬጎን ተቀድማ የብር ሜዳልያ ባለቤት ሆናለች፡፡ በንፅፅር በማጣሪያው ላይ ከተመዘገበው በዘገየ ሰዓት በተጠናቀቀው የፍፃሜ ፉክክር የመጀመሪያው ዙር ቀርፋፋ የነበረ ሲሆን ገንዘቤም ይህን ዙር ከተፎካካሪዎቿ በስተኋላ ሆና ስትከተል ቆይታለች፡፡ በቅድመ ውድድር ዕቅዷ የመጨረሻ ሩጫዋን ስድስት መቶ ሜትር ላይ ልትጀምር አስባ እንደገባች የጠቀሰችው ገንዘቤ ከብር ሜዳልያ ድሏ በኋላ ‹‹በውድድሩ ላይ ቦታ ለመያዝ በነበረው ፉክክር የመጨረሻ ሩጫዬን ቀደም ብዬ 700ሜ. እየቀረኝ ለመጀመር ተገድጃለሁ፡፡ በጉዳት ምክንያት ብዙ ዝግጅት ማድረግ አልቻልኩም እንደዛም ሆኖ ለሀገሬ ብር ሜዳልያ ማምጣት ችያለሁ›› ያለች ሲሆን አሰልጣኟ ጀማ አደን ከአበረታች መድኃኒት ጋር በተያያዘ መጠርጠሩ በእርሷ ላይ ስለፈጠረው ተፅኖ ስታወራም ‹‹በጀማ ጉዳይ በተለይ በሀገራችን ሚዲያዎች ስሜ ሲነሳ ነበር፡፡ ጀማ ተጠረጠረ ማለት እኔ ተያዝኩ ወይም ተጠረጠርኩ ማለት አይደለም፡፡ እኔን ከጀማ ጋር የሚያገናኘኝ ስራ ነው እንጂ ስለዚህ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ይህ ጉዳይ በሀገራችን ሚዲያዎች ትንሽ ጫና አሳድሮብኛል›› ብላለች፡፡ ገንዘቤ በሪዮ ኦሊምፒክ ያሳካችው የብር ሜዳልያ ድል በኢትዮጵያ የ60 ዓመት የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በመካከለኛ ርቀት የተገኘ የመጀመሪያው ሜዳልያ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የኢትዮጵያ የእስከዛሬ የሜዳልያ ድሎች በሁለቱም ፆዎች በ50000ሜ.፣ 10000ሜ.፣ ማራቶን እና 3000ሜ. መሰናክል የተገኙ የነበሩ ሲሆን ገንዘቤ በሪዮ ደ ጃኔይሮ ያመጣችው የ1500ሜ. የብር ሜዳልያ ስኬት የተመዘገበባቸውን የውድድር አይነቶች ቁጥር በአንድ ከፍ ያደረገም ነው፡፡

Read more...

ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የሚሳተፉበት የሪዮ ኦሎምፒክ ፕሮግራም