png-logo-white   GREAT ETHIOPIAN RUN

English Arabic Chinese (Simplified) French German Japanese Norwegian Russian Spanish

አልማዝ አያና በሁለት ርቀቶች (በ10 ሺህ እና 5 ሺህ ሜ.) ትወዳደራለች

በብራዚሏ ሪዮ ደ ጃኔይሮ ከተማ አስተናጋጅነት ከሐምሌ 29 አስከ ነሐሴ 15/2008 ዓ.ም. የሚቆየው የ31ኛው ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ፉክክር በይፋ ሊከፈት ከሶስት ሳምንት ያነሰ ግዜ የቀረው ሲሆን የጨዋታዎቹ ድምቀት እንደሚሆን የሚታመነው የአትሌቲክስ ውድድርም ነሐሴ 6 ቀን የሚጀመር ይሆናል፡፡ በአትሌቲክሱ ዘርፍ በተለይም በረጅም ርቀት የሩጫ ውድድሮች ላይ የስኬታማነት ታሪክ ያለውን የኢትዮጵያ ቡድን እነማን ይወክሉታል የሚለው ጥያቄም ላለፉት ጥቂት ወራት በጉጉት ሲጠበቅ ቆይቶ በሳምንቱ አጋማሽ ብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ይፋ ባደረገው ዝርዝር ምላሽ አግኝቷል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይፋ ያደረገው የሪዮ ኦሊምፒክ ተወዳዳሪ አትሌቶች ዝርዝር 36 ቀጥተኛ ተመራጮች እና 9 ተጠባባቂ አትሌቶች የተካተቱበት ሲሆን በወቅቱ ድንቅ ብቃት ላይ የምትገኘው አልማዝ አያና በሁለት ርቀቶች (በሴቶች 5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር) ሀገሯን ወክላ የምትፎካከር መሆኑንም አረጋግጧል፡፡ በኦሊምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች የከፍተኛ ስኬት ባለቤት የሆነችው እንቁዋ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባም ከረጅም የወሊድ እረፍት መልስ ከሪዮ የ10 ሺህ ሜትር ተፎካካሪዎች ተርታ መግባት የቻለች ሲሆን በሴቶች 5000 ሜትርም በተጠባባቂነት ተመዝግባለች፡፡
በሪዮ ኦሊምፒክ በረጅም ርቀት (5 ሺህ ሜትር እና 10 ሺህ ሜትር) ኢትዮጵያን እንዲወክሉ የተመረጡትን አትሌቶች ወቅታዊ እና ያለፉ እውነታዎችን እንዲሁም ሌሎች ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ ቀጣዩ የቅድመ ምልከታ ዘገባ የኢትዮጵያ የረጅም ርቀት ተወዳዳሪ አትሌቶች በሪዮ ኦሊምፒክ ላይ ሊኖራቸው ስለሚችለው ተሳትፎና ውጤታማ የመሆን ዕድል ለመጠቆም ይሞክራል                


የረጅም ርቀት (5 ሺህ ሜትር እና 10 ሺህ ሜትር) ውድድሮች በኢትዮጵያ የኦሊምፒክም ሆነ የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች የስኬት ታሪክ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ይዘው የሚገኙ እንደመሆናቸው በነዚህ ርቀቶች ውጤት ማምጣት አለመቻል በብዙሀኑ ኢትዮጵያውያን የአትሌቲክስ ደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ የቅሬታ ስሜትን የሚፈጥር መሆኑን በለንደን ኦሊምፒክ እና ባለፉት ሁለት የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ወቅት የተመለከትነው እውነታ ነው፡፡ በአንፃሩም በእነዚህ ርቀቶች የሚመዘገቡ ስኬቶች በሌሎች ርቀቶች ማግኘት ሲገባን የምናጣቸውን ውጤቶች ጭምር የሚያሰረሳ ሲሆንም በብዙ አጋጣሚዎች ተስተውሏል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ1956ቱ የሜልቦርን ኦሊምፒክ አንስታ በሁሉም የውድድር አይነቶች ባደረገቻቸው 12 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተሳትፎ 21 የወርቅ፣    7 የብር እና 17 የነሐስ በድምሩ 45 ሜዳልያዎች 34ቱ (15 የወርቅ፣ 7 የብር እና 12 የነሐስ) በሁለቱ ርቀቶች ብቻ የተመዘገቡ መሆናቸውም እውነታውን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ የቁጥር ማስረጃ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በብራዚል ሪዮ ደ ጃኔይሮ 13ኛ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ በ5 ሺህ ሜትር እና 10 ሺህ ሜትር በምታደርገው ፉክክር የሚወክሏት አትሌቶች ከቅርብ ዓመታት (ከለንደን ኦሊምፒክ) ወዲህ በተለይም በወንዶች እየራቀን የመጣውን ውጤት የመመለስ ትልቅ ኃላፊነትን ለመወጣት አብዝተው መታተር ይጠበቅባቸዋል፡፡
የወንዶች 10 ሺህ ሜትር
በሪዮ ኦሊምፒክ የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ተወካዮቻችን (ይግረም ደመላሽ፣ ታምራት ቶላ እና አባዲ ሀዲስ) በለንደን ኦሊምፒክም ሆነ ከዛ በኋላ በተደረጉት ሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች ላይ ያልታዩና አዲስ ሊባሉ የሚችሉ ወጣት አትሌቶች ሲሆኑ የ2011 የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ ባለቤቱ ኢብራሂም ጄይላንም በተጠባባቂነት ተይዟል፡፡ በ45ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመጀመሪያ ግዜ ባደረገው የ10 ሺህ ሜትር ተሳትፎ አሸናፊ ለመሆን ከበቃ ወዲህ በ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር በተካፈለባቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲሁም በሄንግሎ በተደረገው የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የ10 ሺህ ሜትር ሰዓት ማሟያ ውድድር ወጥ የሆነ ምርጥ አቋም በማሳየት በርቀቱ በዋና ተመራጭነት በ5 ሺህ ሜትር በተጠባባቂነት የተመረጠው ወጣቱ አባዲ ሀዲስ ከዕድሜ ማነስ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በዋናነት በተመረጠበት የ10 ሺህ ሜትር ውድድር ላይ መሳተፍ ይቻል አይቻል ይህ ዘገባ እስከተሰራበት ሰዓት ድረስ የተረጋገጠ ነገር የሌለ ሲሆን ጉዳዩን በተመለከተ ከብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ታምራት በቀለ ባገኘነው መረጃ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ለዓለም አቀፉ የስፖርቱ አስተዳዳሪ አካል ጥያቄ አቅርቦ ምላሹን እየተጠባበቀ እንደሚገኝና በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ለውሳኔ የሚረዳቸውን ምላሽ እንደሚያገኙ ማወቅ ችለናል፡፡ ውሳኔው አባዲ በዕድሜው ማነስ ምክንያት በ10 ሺህ ሜትር መፎካከር አይችልም የሚል ከሆነም ተጠባባቂው ኢብራሂም ጄይላን እርሱን ተክቶ እንደሚወዳደር ይጠበቃል፡፡
በኦሊምፒክ የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ውድድር ለወትሮው የተለመደው ተጠባቂ ፉክክር በኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን አትሌቶች መካከል ይደረግ የነበረ ቢሆንም ከ2011 የዴጉ ዓለም ሻምፒዮና ወዲህ ተጠባቂው ነገር ኬንያውያን እና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነቱን ከትውልደ ሶማሊያዊው እንግሊዛዊ ሞ ፋራህ ይነጥቁታል ወይ ወደሚል ጥያቄነት ተቀይሯል፡፡ በሪዮ ኦሊምፒክም በርቀቱ ስለሚደረገው ፉክክር ከወዲሁ እየተነሱ ያሉ የመወያያ ርዕሶች በለንደን ኦሊምፒክ እና ባለፉት ሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች ላይ የወርቅ ሜዳልያውን አላስቀምስ ያለው ሞ ፋራህ በኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን አትሌቶች ላይ እያሳየ ባለው የበላይነት ይቀጥላል ወይስ የቀድሞዎቹ የርቀቶቹ ንጉሶች ክብራቸውን ያስመልሳሉ በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ በኩል በ2012 ባርሴሎና ላይ የዓለም ወጣቶች የ10 ሺህ ሜትር ሻምፒዮን ከሆነ በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከጉዳት ጋር በተያያዘ ስኬታማ የውድድር ተሳትፎ ያልነበረው እና ባለፈው ወር በኔዘርላንድ ሄንግሎ በተከናወነው የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሰዓት ማሟያ ውድድር የራሱን ምርጥ ባሻሻለበት 26፡51.11 አንደኛ ወጥቶ የመጀመሪያ ተመራጭ የሆነው ይግረም ደመላሽ፣ በ2015 በቻይና ጉያንግ የዓለም ሀገር አቋራጭ ውድድር ላይ የቡድን ወርቅ ሜዳልያ ማስገኘት ከቻሉት አትሌቶች መካከል አንዱ የነበረው እና በዘንድሮው የታላቁ ሩጫ የጎዳና ላይ 10 ኪ.ሜ. ውድድር አሸናፊ የሆነው ታምራት ቶላ እንዲሁም ብዙም እውቅና የሌለው አዳዲ ሀዲስ ወይም ኢብራሂም ጄይላን በሪዮ ኦሊምፒክ ስታድየም ከሞ ፋራህ እና ከኬንያውያኑ ተቀናቃኞቻቸው (ፖል ታኑዪ፣ ቻርልስ ዮሴይ፣ ጂኦፍሬይ ካምዎሮር እና ቤዳን ካሮኪ) ጋር የሚያደርጉትን ውድድር በአሸናፊነት ለመወጣት ትልቅ የስነልቦና ጥንካሬ እና የታክቲክ አተገባበር ብቃትን ተላብሰው መቅረብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን አሰልጣኞቻቸውም አትሌቶቹ በሻምፒዮንሺፕ ውድድር ላይ ሊኖራቸው የሚገባውን የአሸናፊነት መንፈስ እንዲላበሱ እና በታክቲክ አተገባበሩ ረገድ ከተፎካካሪዎቻቸው የላቁ እንዲሆኑ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ በሪዮ ኦሊምፒክ የ10 ሺህ ሜትር ፉክክር ሞ ፋራህ አሁንም የአሸናፊነቱን የግንባር ቀደም ግምት እያገኘ ያለ አትሌት ሲሆን ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን አትሌቶች ለሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃዎች እንደሚፎካከሩ ይገመታል፡፡ 

የወንዶች 5 ሺህ ሜትር
Rio Olympic 5000m Men teamየ5 ሺህ ሜትር ወንዶች ውድድርም የአትሌቲክስ ረጅም ሩጫ ብርቱ ተቀናቃኞች ኢትዮጵያ እና ኬንያ አትሌቶች ከእንግሊዛዊው ሞ ፋራህ ጋር የሚፋለሙበት ሌላ የፍጥጫ መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ለ5 ሺህ ሜትር ወንዶች ተወካይነት የመጀመሪያ ተመራጭ ከሆኑት ሶስት አትሌቶች መካከል ሁለቱ ከአራት ዓመት በፊትም በለንደን ኢትዮጵያን ወክለው ቀርበው የነበሩት ደጀን ገ/መስቀል እና ሀጎስ ገ/ሕይወት ሲሆኑ በርቀቱ የወቅቱ ምርጥ አቋም ባለቤት ሙክታር እድሪስም የመጀመሪያ የኦሊምፒክ ተሳትፎውን የሚያደርግ ይሆናል፡፡ በለንደን ኦሊምፒክ የ5 ሺህ ሜትር የፍፃሜ ውድድር ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳልያ ተሸላሚ የሆነው ደጀን ገ/መስቀል የመጨረሻው ዙር ላይ የመስመር አያያዝ ስህተት ባይሰራ ኖሮ በወቅቱ ሞ ፋራህን ማሸነፍ የሚችልበት አቅሙ ነበረው፡፡ ደጀን ከለንደን ኦሊምፒክ በኋላ በተደጋጋሚ የአቋም መዋዠቅ ይታይበት የነበረ ቢሆንም የኦሊምፒክ ፉክክር በሚደረግበት ዓመት ዳግም አቋሙን አስተካክሎ ብቅ ያለ ይመስላል፡፡ በለንደን ኦሊምፒክ የ5 ሺህ ሜትር ፍፃሜ 11ኛ ሆኖ ማጠናቀቁን ተከትሎ ባለፉት ሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች (ሞስኮ እና ቤይጂንግ) ላይ በርቀቱ የብር እና የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊ መሆን የቻለው ሀጎስ ገ/ሕይወት ባለፈው ዓመት በዶሀ ዳይመንድ ሊግ የ3000ሜ. ፉክክር በሞ ፋራህ ላይ የተጎናፀፈውን ድል በሪዮ ስለመድገም እያለመ እንደሚዘጋጅ ይታመናል፡፡ በ5 ሺህ ሜትር በ2015 እና በዘንድሮው ዓመት የፈጣኑ ሰዓት ባለቤት መሆን የቻለው ሙክታር እድሪስ ባለፈው ዓመት የርቀቱ ፈጣን ሰዓት ባለቤት የነበረ ቢሆንም በቤይጂንጉ ዓለም ሻምፒዮና በሄንግሎ በተደረገው የኢትዮጵያውያን መምረጫ ውድድር አሸናፊ በነበረበት 10 ሺህ ሜትር ለመወዳደር መምረጡ ብዙዎችን ያስገረመ ጉዳይ ነበር፡፡ የ2016 የቤት ውጭ አትሌቲክስ ውድድሮች መካሄድ ከጀመሩበት ግንቦት መጀመሪያ አንስቶ በሻንግሀይ እና ዩጂን የ5000ሜ. የወቅቱን የዓለም አንደኛ እና ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ የቻለው ሙክታር ዘንድሮ በተወዳደረባቸው ሌሎች ውድድሮችም ያልዋዠቀ አቋም በመያዝ የርቀቱ የዳይመንድ ሊግ የነጥብ ፉክክር የበላይነትን እንደያዘ ወደ ሪዮ ለማቅናት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
ሞ ፋራህ በ10 ሺህ ሜትር ላይ ከተወዳደረ በኋላ የማጣሪያ ውድድር ላይ በመሳተፍ ጭምር በሚያደርገው በዚህ ፉክክር ሶስቱ ኢትዮጵያውን እና ኬንያዊው ካሌብ ንዲኩ ካላቸውም ልምድ አንፃር የማሸነፍ ዕድሉ ይኖራቸዋል ተብሎ ይታመናል፡፡          

የሴቶች 10 ሺህ ሜትር
Rio Olympic 10000m Women teamበሴቶቹ 10 ሺህ ሜትር በኩል በኦሊምፒክ ውድድር የመጀመሪያ ተሳትፎዋን የምታደርገው የወቅቱ ድንቅ አልማዝ አያና እንዲሁም በኦሊምፒክም ሆነ በዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ተሳትፎ የተካበተ ልምድና የስኬት ታሪክ ያላቸው ጥሩነሽ ዲባባ እና ገለቴ ቡርቃ ይገኛሉ፡፡ ይህ ውድድር የከፍተኛ ስኬት ባለቤቷ ኢትዮጵያዊት ድንቅ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የእርሷን ፈለግ በመከተል ተመሳሳይ ታሪክን ለመድገም በመንደርደር ላይ ከምትገኘው ሌላኛዋ ድንቅ ኢትዮጵያዊት ወጣት አትሌት አልማዝ አያና ጋር ለወርቅ ሜዳልያው የሚፎካከሩበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ባለፈው ዓመት በቻይና ቤይጂንግ በተከናወነው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በቅደም ተከተል የወርቅ እና ብር ሜዳልያ ባለቤት የሆኑት ኬንያዊቷ ቪቪያን ቼሪዮት እና ኢትዮጵያዊቷ ገለቴ ቡርቃም ከጠንካራ ተፎካካሪዎቹ ተርታ ከሚመደቡ አትሌቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የሴቶች 10 ሺህ ሜትር ኢትዮጵያውያን በሪዮ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳልያን እንደምናገኝ በእርግጠኝነት ልንናገር ከምንችልባቸው ውድድሮች አንዱ እንደሆነም ይታመናል፡፡ ቤትሲ ሳንያ እና የአፍሪካ ሻምፒዮኗ አሊስ አፕሮት በኬንያውያን እና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል የሚደረገው ፉክክር አድማቂ የሚሆኑ ሌላኛዎቹ ኬንያውያን ናቸው፡፡
ጥሩነሽ ዲባባ ያለፉት ሁለት ኦሊምፒኮች የርቀቱ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤት እንደመሆኗ በሪዮ ይሄን ገድል በተከታታይ ለሶስተኛ ግዜ በመፈፀም ከዓለም ብቸኛዋ አትሌት የመሆን ታሪክን ስለማስመዝገብ ስታልም ወጣቷ አልማዝ (በ5 ሺህ ሜትርም ስለምትወዳደር) በበኩሏ ጥሩነሽ በ2008ቱ የቤይጂንግ ኦሊምፒክ ያስመዘገበችውን የድርብ ድል ገድል መፈፀምን ትሻለች፡፡ 

የሴቶች 5 ሺህ ሜትር
Rio Olympic 5000m Women teamእ.አ.አ በ2012 በለንደን ለተካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር በ3000ሜ. መሰናክል ለመመረጥ ተቃርባ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ ሳይሳካላት ቀርቷል፡፡ ይህ በመሆኑ ተስፋ ያልቆረጠችው አልማዝ አያና ከ2013 አንስታ የምትወዳደርበትን ርቀት ከ3000ሜ. መሰናክል ወደ 5000ሜ. በመቀየር ላለፉት ሶስት ዓመታት በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ ትልልቅ ስኬቶችን መጎናፀፍ የቻለች ሲሆን እነሆ ከአራት ዓመት ጠንካራ ስራ በኋላም በሪዮ ኦሊምፒክ በሁለት ርቀቶች ሀገሯን መወከል የሚያስችላትን ዕድል አግኝታለች፡፡ ከቤይጂንጉ የዓለም ሻምፒዮና በፊት ከአልማዝ ጋር በነበረኝ የቃለ ምልልስ ቆይታ የእነ ጥሩነሽ እና መሰረት ተተኪ ተብላ መነፃፀሯ ያስፈራት እንደሁ ጠቅሼ ለሰነዘርኩላት ጥያቄ ‹‹የእነዚህ ታላላቅ አትሌቶች ተተኪ ተብዬ መነፃፀሬ ያስደስተኛል እንጂ አያስፈራኝም፡፡ እንዲያውም እግዚአብሔር ቢፈቅድ ዕቅዴ ከእነርሱም በላይ የሆነ ስኬትን ማስመዝገብ ነው›› የሚል ምላሽን ሰጥታኝ የነበረ ሲሆን ቤይጂንግ ላይ የዓለም ሻምፒዮን ከሆነችበት ድንቅ ብቃት ቀጥሎ በሪዮ ኦሊምፒክ እውነተኛ ተተኪነቷን የምታረጋግጥበትን ሌላ ገድል ልትፈፅም እንደምትችል ይጠበቃል፡፡
አልማዝ ከቤይጂንግ ዓለም ሻምፒዮና በኋላ በሰጠችኝ ሌላ አስተያት ስለቀጣይ ዕቅዷ ስትናገር ‹‹በሪዮ ኦሊምፒክ ላይ በሁለት ርቀቶች (በ5000ሜ. እና 10000ሜ.) ሀገሬን መወከል እና ስኬታማ መሆን እፈልጋለሁ›› ብላ የነበረ ሲሆን የሴቶች 5000ሜ. የዓለም ሪኮርድን ስለመስበር ስታወራም ‹‹ጠንክሮ ከተሰራ የማይቻል ነገር አይደለም፡፡ ከተቻለ ደግሞ እኔም ሪኮርዱን የማሻሻል ሀሳቡ አለኝ›› በማለት አክላ ነበር፡፡ ከዚህ አስተያየቷ በኋላ የርቀቱን የዓለም ሪኮርድ የመስበር ተደጋጋሚ የተቃረቡ ሙከራዎችን በማድረግ የራሷን ምርጥ ሰዓቶች ማሻሻል የቻለችው አልማዝ በተለይም በዘንድሮው የሮም ዳይመንድ ሊግ ስታሸንፍ በጥሩነሽ ዲባባ የተያዘውን 14፡11.15 የሆነ የዓለም ሪኮርድ እጅጉን የተቃረበ፣ የዓለም የምንግዜም ሁለተኛው ፈጣንና የራሷ ምርጥ የሆነ 14፡12.59 ሰዓት አስመዝግባለች፡፡ አልማዝ ቀደም ብላ በ10 ሺህ የፍፃሜ ውድድር ላይ የምትካፈል መሆኑ ከሚፈጥርባት ድካም በፍጥነት የማገገም ወይም የጉዳት ችግር ካልገጠማት በስተቀር በዚህኛውም ርቀት የወርቅ ሜዳልያው የኢትዮጵያ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ሰንበሬ ተፈሪ እና አባበል የሻነህ ከአልማዝ ጋር በሪዮ ኦሊምፒክ የቤይጂንጉን ዓለም ሻምፒዮና ገድል ለመድገምና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ከፍ ለማድረግ የሚወዳደሩ ሲሆን ጥሩነሽ ዲባባም የርቀቱ ተጠባባቂ ሆና ተመዝግባለች፡፡ በኬንያ በኩል ቪቪያን ቼሪዮት፣ ከወሊድ የተመለሰችው የቀድሞዋ 1500ሜ. ተወዳዳሪ ሔለን ኦቢሪ እና ሜርሲ ቼሮኖ የእነአልማዝ ብርቱ ተቀናቃኞች እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡

Share